ቀጥታ፡

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 15/2015 የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያሳድጉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ዘርፉ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮችን የያዘ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በመድኃኒት ማምረት፣ በግንባታ እቃዎች እና ሲሚንቶ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ከተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ‘CHAIRMAN Chongqing Pharmaceuticals Holding’፣ ‘BieGen’፣ ‘CNBM’፣ ‘SINOMA Engineering’ እና ‘SINOMA Cement Company Ltd’ ከተሰኙ ድርጅቶች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በቤጂንግ ውይይት አድርገዋል።

ኮሚሽነሯ ከ‘CHAIRMAN Chongqing Pharmaceuticals Holding’ እና ‘BieGen’ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካልስ አንዱስትሪ ፓርክም ዘመናዊ እና ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እንዲገቡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች እና የዘርፉ ተዋናዮች ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ከ ‘SINOMA Engineering’ እና ‘SINOMA Cement Company Ltd’ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ ባለው ከፍተኛ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ምክንያት በግንባታ እቃዎች እና ሲሚንቶ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን መኖሩን ገልጸው፤ ይሄም በዘርፎቹ ለሚሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ ኮሚሽነሯ አመስግነው በማምረቻ ዘርፍ በይበልጥ እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም