ሰላምን ለመጠበቅና ለማጎልበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል - የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለመጠበቅና ለማጎልበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል - የሰላም ሚኒስቴር
አዳማ የካቲት 15/2015(ኢዜአ) ሰላምን መጠበቅና ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሆን ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ አስገነዘቡ።
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርሲቲያን የልማት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሰላም ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የሰላም ግንባታ ለሀገራችን እጅጉን አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
"ሰላምን መጠበቅና ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካላት መሆን አለበት" ያሉት አቶ ታዬ ዜጎች ይሄንን ተገንዝበው ለሰላም ግንባታ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ማህበረሰቡ የሰላም ግንባታ ማዕከል እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል አቶ ታዬ።
"በማህበረሰቦች ማካከል የሚኖረው አለመግባባትና ግጭቶች አብዛኞቹ በውይይቶች የሚፈቱ ናቸው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በየተቋማቱ የፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን ከማምከን ጀምሮ በተለይ ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ፎረምና ክበባት በማደራጀት ብቁ፣ በስነ ምግባር የታነፀና በውይይት የሚያምን ትውልድ እንዲገነባ ማስቻል አለብን ብለዋል።
በዚህም በተማሪዎች መካከል የመነጋገር፣ የአብሮነት፣ አንድነት፣ መተማመንና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌዎችና ባህሎች ይበልጥ እየዳበሩ ይሄዳሉ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እምሩ ሙላቱ በበኩላቸው ሰላም ከሌለ ማምለክ፣ ሰርቶ መለወጥና ወጥቶ መግባት የለም ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በልማት ኮሚሽኗ አማካይነት በሰላም ግንባታ ላይ የራሱዋን ድርሻ ለማበርከት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እየሰራች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
አሁን በተፈጠረው ምቹ የበጎ አድራጎት ህጎችና አሰራሮች በመጠቀም በሰላም ግንባታ፣ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ከ160 በላይ ፕሮጄክቶች በ11 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ አንድነትን፣ መልካምነት፣ አብሮነትና ሰላምን በማፅናት ላይ የድርሻዋን እያበረከተች መሆኑንም አመልክተዋል።