ቀጥታ፡

ኢዜአ በአገሪቱ የመረጃ ልውውጥና ተደራሽነትን ለማሳለጥ የሚያበርክተው አስተዋጽዖ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 15/2015…የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአገሪቱ የመረጃ ልውውጥና ተደራሽነትን ለማሳለጥ የሚያበርክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።

ሥልጠናው ለአንድ ወር የተዘጋጀ ሲሆን የተግባቦት ጽንሰ ሃሳብ፣ መረጃን ማደራጀትና ማሰራጨት፣ መልዕክት ቀረጻ፣ የፊቸር አጻጻፍ እንዲሁም የተግባቦት ስትራቴጂዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በመረጃ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ተቋማትን አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።

አገራዊ ግቦችን ለማሳካት ጠንካራ የመረጃ ሥርዓትና አቅሙ የተገነባ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል።

ሠልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታ ለሥራቸው ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል እውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ተቋማዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት እገዛ እንደሚያደርግላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢዜአም ሥልጠናውን ለሰባተኛ ጊዜ እየሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው መሰል የሥልጠና መድረኮች የልምድ ልውውጥና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በአገሪቷ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መረጃ የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመው የመረጃ ልውውጡና ተደራሽነቱን ለማሳለጥ ኢዜአ የሚያበረክተውን አሰተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት ዳይሬክተር አቶ ማንአየህ ዓለሙ በበኩላቸው ማንኛውም ዜጋ መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው በሕግ የተደነገገ መሆኑን አመልክተው ተግባራዊ እንዲሆን የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ትልቅ መሆኑን ጠቁመው ይሄን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

መረጃዎች ከአገር ሉዓላዊነት አኳያ፣ ከህዝብ ጥቀም አንጻር በአግባቡ መቃኘት እንደሚገባ ጠቁመው እነዚህን መሰረታዊ ክህሎቶች ተደራሽ በማድረግ ረገድ መሰል ሥልጠናዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ኢዜአ ባለፉት ስድስት ወራት ለስድስት ዙር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመልዕክት ዝግጅትና ንግግር ጹሁፍ አዘገጃጀት፣ በፊቸር አጻጻፍ፣ በምስልና ድምጽ ቀረጻ፣ በምስልና ድምጽ ኤዲቲንግ፣ በመጽሄት አዘገጃጀት እንዲሁም በተቋማዊ መለያ/ብራንዲንግ/ ርዕሶች ዙሪያ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ የፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢኒስቲትዩት፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ሥልጠናውን የወሰዱ ተቋማት ናቸው።

አሁን እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ ደግሞ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከመስኖናና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት፣ ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንና ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተውጣጡ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም