ኢትዮጵያን በዓለም እያስተዋወቀ ያለው ሰርከስ የመለማመጃ ቦታ እጥረት እየገጠመው ነው-ብሔራዊ ሰርከስ ጥምረት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በዓለም እያስተዋወቀ ያለው ሰርከስ የመለማመጃ ቦታ እጥረት እየገጠመው ነው-ብሔራዊ ሰርከስ ጥምረት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 15/2015 ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች እያስተዋወቀ የሚገኘው የሰርከስ ጥበባዊ እንቅስቃሴ የመለማመጃ ቦታ እጥረት እየገጠመው መሆኑን የብሔራዊ ሰርከስ ጥምረት ገለጸ።
የአካልና የአዕምሮ ዝግጁነትና ብቃት የሚጠይቅና በግልና በቡድን የሚሰራው የሰርከስ ጥበባዊ እንቅስቃሴ በተለይም በውጭው ዓለም ትልቅ ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያም የሰርከስ ጥበብ ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም በዘመናዊ መልኩ የተጀመረው ግን በ1984 ዓ.ም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ "ሰርከስ ኢትዮጵያ" በሚል መጠሪያ የተጀመረው ዘመናዊ የሰርከስ ጥበብ ከዚያ በኋላ ወደ ሌሎች ክልሎች አድማሱን ማስፋቱ ነው የሚነገረው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ጥምረት ፕሬዝዳንት ተክሉ አሻግር፤ ሰርከስ በኢትዮጵያ በዘመናዊ መልኩ ከተጀመረ በኋላ በፍጥነት እያደገ የመጣ ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህም በርካታ ወጣቶችና ታዳጊዎች በመልካም ሰብዕና ተቀርጸው እያደጉበት ያለ የጥበብ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን የሰርከስ ጥበብ ሥራዎቻቸውን በተለያዩ ሀገራት በማቅረብ እየተደነቁበትና የአገራቸውንም ስም እያስጠሩበት ያለ ዘርፍ መሆኑን አቶ ተክሉ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቅና የአገር ገጽታን በመገንባት ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለራሳቸው ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል ነው ያሉት።
በዓመት በአማካይ እስከ 500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሰርከስ ጥበብ አቅራቢዎች በተለያዩ ሀገራት ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል።
የሰርከስ ጥበብ ዘርፍ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታና የውጭ ምንዛሬ ግኝት የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ያለው የሰርከስ እንቅስቃሴ ራሱን የቻለ ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኖ እንዲወጣ መሥራት እንደሚገባ አቶ ተክሉ ገልጸዋል።
በተለይ ለሰርከስ ጥበበኞች የልምምድ መሥሪያ ቦታ ችግር መኖሩ ዘርፉን እየጎዳው ነው ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሰርከስ የልምምድ መሥሪያ ቦታና ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ የመግባት ሁኔታዎች ቢመቻቹ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት።