የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ በይፋ ለማስጀመር አብዛኛዎቹ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 15/2015 የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ (የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን) በይፋ ለማስጀመር አብዛኛዎቹ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሕግ አማካሪ በሱፍቃድ ተረፈ ገለጹ።

በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በገበያው ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው ብለዋል።

የካፒታል ገበያ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ተዛማጅ ውሎች የመሳሰሉ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት የሚከናወንበት ቦታ ነው።

ኢትዮጵያም ባደጉት ሀገራት በስፋት የተተገበረውን የካፒታል ገበያን ወደ ስራ ለማስገባት አዋጅ 1248/2013ን አፀድቃ እንቅስቃሴ ጀምራለች።

የአዋጁን መውጣት ተከትሎም የካፒታል ገበያውን ለማስጀመር በብሔራዊ ባንክ ስር ፕሮጀክት ተቋቁሞ ለአንድ ዓመት ያህል ሲሰራ ቆይቷል።

በብሔራዊ ባንክ ስር ሲንቀሳቀስ የቆየው ቡድንም ስራውን በቅርቡ ለተቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በማስረከብ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የህግ አማካሪ በሱፍቃድ ተረፈ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማስጀመር አብዛኛዎቹን ዝግጅቶች በማጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።

ለዚህም የሚያግዙ ስምንት መመሪያዎችና ደንቦች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ ኢንቨስተሮችም እንዲወያዩባቸው በማድረግ ተጨማሪ ግብዓት መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የካፒታል ገበያ አዋጁ ለባለ ስልጣኑ በሰጠው ስልጣን መሰረት የካፒታል ገበያውን ለማስተዳደር የሚያስችሉ መመሪያዎች መውጣታቸውም እንዲሁ ።

ሌሎችም መመሪያዎች አሉ፤ ኪሳራዎችን መተካት የሚቻልበት የካሳ ፈንድ ደንብ፣ ሌሎችም ተዘጋጅተው ለመፅደቅ በዝግጅት ላይ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያውን ለማስጀመር በዙ ስራዎች መጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ስለ ካፒታል ገበያው ከውጭ ተቋማት ጋር በመተባበር በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለድርሻዎች ስለገበያው ፋይዳና አተገባበር በቂ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንም ነው ያነሱት።

የህግ አማካሪው አክለውም፤ የተዘጋጁት መመሪያዎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ አዋጁ እውቅና የተሰጠው ቢሆንም ሂደቱን መምራት፣ መቆጣጠርና መደገፍ የሚያስችል መመሪያ እንደተዘጋጀለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ደላላ፣ የገበያ አከናዋኝ፣ የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የውክልና አስተዳዳሪዎች፣ የጋራ ኢንቨስትመንት ባንክ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ በካፒታል ገበያው አገልግሎት ለሚሰጡ 15 ዘርፎችም ፈቃድ መስጠት የሚያስችሉ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ለመሳተፍ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑንም አቶ በሱፍቃድ ገልጸዋል።

በተለይም በውጭ የካፒታል ገበያዎች ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገበያው ሲጀመር በኢንቨስትመንትና በልዩ ልዩ መስኮች ለመሳተፍ እውቀታቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ነው ብለዋል።

የካፒታል ገበያው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማንሳት አምራች ኢንዱስትሪዎች ኢንዱስትሪዎች ያላቸውን የብድር ሰነድ ካፒታል ገበያው ላይ በመሸጥ ካፒታላቸውን የሚያሳድጉበት እድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።

ለባንኮችና ለመንግስት አማራጭ የገንዘብ ማግኛ ከመሆኑም በላይ ቁጠባን በማሳደግ በብድር የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለማከናወን፣ የክፍያ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛንን የማስተካከል ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም