የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የበኩሉን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የበኩሉን እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናገሩ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአየር ትራንስፖርት የንግድና ኢኮኖሚ ትስስርን ለማፋጠን ወሳኝ ነው።
ይህንን ከግምት በማስገባት አየር መንገዱ ያደረገው የማስፋፊያ ሥራ በተለይም ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ዋነኛ መዳረሻና መተላለፊያ መስመር ማድረጉን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቱ ያለውን የበረራ መዳረሻ በማስፋፋት የአፍሪካ ኅብረት የጀመረውን ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣን የአየር መንገዱን የመዳረሻ፣ የንግድና የአገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋትም ተጨማሪ እድል ማምጣቱንም ገልጸዋል።
የኬኒያ ሲቪል አቬየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ካፒቴን ካልበርት ክቤ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን ንግድና ቱሪዝም በማስተዋወቅ የአህጉሪቷን ትስስር በማሳለጥ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።
አየር መንገዱ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በመተባባርም ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
አየር መንገዱ በ2020 በሰጠው ውጤታማው የፓን አፍሪካኒዝም የአየር ትራንስፖርትና የጭነት አገልግሎት አንደኛ ደረጃ ማግኘቱ የስኬቱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት አህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማሳለጥ በሚል አንድ ወጥ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግም የኅብረቱ የ2063 ዋና አጀንዳ ነው።