ኢትዮጵያ እና ቻይና የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ቡድን ለመመሥረት ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ቡድን ለመመሥረት ስምምነት ተፈራረሙ
የካቲት 14/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ቻይና የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን የትግበራ ቡድን ለመመሥረት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቻይና ቤጂንግ የገቡት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ እና የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሊ ፌይ መፈራረማቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።
ቡድኑ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ግንኙነታቸውን በስትራቴጂካዊ መስኮች በጋራ የማሳደግ ዓላማን ያነገበ መሆኑ ተገልጿል።
በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቤጂንግ መግባታቸው ይታወሳል።
ልዑኩ በኢትዮጵያ እና ቻይና የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚ ትብብር ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።