ከፊታችን ለሚጠብቁን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለብን - ኢዜአ አማርኛ
ከፊታችን ለሚጠብቁን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለብን
የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ከፊታችን ለሚጠብቁን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለብን ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለፁ።
በ44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብር አከናውኗል፡፡
በዕውቅና መርሐ ግብሩ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች 45 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላስመዘገቡት 30 ሺህ ብር፣ ለነሐስ ሜዳሊያ 15 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡ 10 ሺህ ብር እና ተሳትፎ ላደረጉ አትሌቶች 5 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
አትሌት ለተሰንበት ግደይ ደግሞ ልዩ ተሸላሚ በመሆን ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ሽልማት ተበርክቶላታል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉት፤ በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ የተካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ፈታኝ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የነበረውን አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ተቋቁመው ኢትዮጵያን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ እንድትገባ አድርገዋታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ከኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ሆና ብታጠናቅቅም፤ ከጠበቅነው አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል።
በቀጣይ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማምጣት አትሌቶችና ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በጠንካራ የቡድን ስራ ለተገኘው ውጤት አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ በተደረገው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ በ7 ብር፣ በ1 ነሐስ፣ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች በመሰብስብ ኬንያን በመከተል በሁለተኛነት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡