ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል በዓል አገራዊ ክብርንና አንድነትን በሚያሳይና ወጥነት ባለው መልኩ በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል

የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የዓድዋ ድል በዓል አገራዊ ክብርንና አንድነትን በሚያሳይና ወጥነት ባለው መልኩ በብሔራዊ ደረጃ የሚከበር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ለሆነው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ተነስተው የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ኃይል በመዋጋት ድል ያደረጉበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑ ይታወቃል።

የዓድዋ ድል በዓል ከኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ባለፈ የመላው የጥቁር ሕዝቦች የድል አድራጊነት ብሥራት የታወጀበት እለትም ነው።

በመሆኑም የዘንድሮው 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያን ክብርንና አንድነትን በሚያሳይና ወጥነት ባለው መልኩ በብሔራዊ ደረጃ የሚከበር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያውያን የአንድነት ተጋድሎ የተገኘ አንጻባራቂ ድል በመሆኑ የሁሉም ኩራት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የቀደሙት ትውልዶች ለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ በጋራና በጀግንነት ዋጋ በመክፈል የኢትዮጵያን ነፃነት በማስጠበቅ ለትውልድ ያሸጋገሩበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ወጥነት ባለው መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ለበዓሉ አከባበር ስኬታማነት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በጋራ እና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለበዓሉ አከባበር በተበጣጠሰ መልኩ በግል መርሃ-ግብሮችን ማዘጋጀት ሳይሆን ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በመሆን በጋራ ማክበር ይገባልም ነው ያሉት።

የበዓሉን አከባበር ለገንዘብ ማግኛ መንገድ የሚጠቀሙ አካላት እንዳሉ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ እነዚሁ አካላት ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም በዓሉን ለማክበር በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝግጅቶች ስለማይኖሩ ሁሉም ዝግጅቶች በማዕከላዊነት በጋራ የሚከበሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደመው ትውልድ ሁሉ ለአገር አንድነትና ብሔራዊ ኩራት የጋራ አቋም በመያዝ ያለፈውን ታሪክ በመረዳት ለራሱም ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ መሥራት አለበት ብለዋል።

የአገርን አንድነት ማስጠበቅ፣ አገርን መውደድ እና የአገር ፍቅርን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ አደራ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት” በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 23 የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም