ቀጥታ፡

የድሬዳዋ አስተዳደር በኢንተርፕራይዝ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶችን በመደገፍ አበረታች ለውጥ እየተገኘ መሆኑን ገለጸ

ድሬዳዋ፤ የካቲት 14 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ አስተዳደር በኢንተርፕራይዝ ዘርፎች የተሰማሩ አንቀሳቃሽ ወጣቶችን በብድር አገልግሎትና በማምረቻ ቦታ አቅርቦት በመደገፍ አበረታች ለውጥ እየተገኘ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በድሬዳዋ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ሲጀመር የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንዳሉት፤ የኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾችን በዘመናዊ ስልጠና ብቃታቸውን በማሳደግ የሚፈለገውን የምጣኔ ሃብት ሽግግርን ለማሳካት መረባረብ ያስፈልጋል።

በድሬዳዋ በዘርፉ የተሰማሩ የወጣቶችን በስልጠና፣ በብድር አገልግሎትና በማምረቻ ቦታ አቅርቦት በመደገፍ አበረታች ለውጥ እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል ።

ይህን ይበልጥ ለማሳደግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እየሰጠ የሚገኘው የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በቀጣይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አስተዳደሩ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ባንክ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ደምሴ በበኩላቸው፤ በተዘጋጀው አራተኛው ዙር ስልጠና በድሬዳዋ በዘርፉ የተሰማሩ 1ሺህ 300 በወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የተዘጋጀው ስልጠና በቀጣይ የተሻለ ለመስራት መነቃቃት የፈጠረና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በስልጠናው ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ የድሬደዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት፣ ዘርፉን የሚመሩ ሴከተሮችና የልማት ድርጅቶች አመራሮች መገኘታቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም