ቀጥታ፡

የሐረሪ ክልል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ሐረር፣ የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የሚሰጠው ስልጠና ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር በሀረሪ ክልል ለሚገኙ ከ2 ሺህ 200 በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በዛሬው እለት ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ ስልጠናው የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማጎልበት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሃብት የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም በክልሉ ለሚገኙ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ወደ ተግባር ተቀይሮ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግብ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ራሳቸውንና አገራቸውን ሊጠቅም የሚችል ስራ ለመስራት ዝግጁ እንዲሆኑ አመልክተዋል።

በሀረሪ ክልል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሃላፊ አቶ ከበደ አዱኛ ስልጠናው ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ የቢዝነስ እቅድ አዘገጃጀት፣ የብድር ፖሊሲ እና የመሳሰሉት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን ወስደው አዋጭ የሆነ የስራ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ለሚያቀርቡ ወጣቶች በባንኩ በኩል የገንዘብ አቅርቦት እንደሚመቻች ጠቁመው፤ የተቀሩትንም በተለያዩ ዘርፎች በማደራጀት በ 5 ሺህ ብር ክፍያ በአክሲዮን ተደራጅተው የስራ ባለቤት የሚሆኑበትን እድል መመቻቸቱን ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ተመዝጋቢዎች ስልጠናውን በ 3 ዙር እንደሚወስዱ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም