የምርጥ ዘር አዋጅ ማሻሻያው ለአርሶ አደሩ ዘርን በተሻለ መልኩ ማቅረብ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የምርጥ ዘር አዋጅ ማሻሻያው ለአርሶ አደሩ ዘርን በተሻለ መልኩ ማቅረብ ያስችላል
አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 14/2015 የምርጥ ዘር አዋጅ ማሻሻያው አርሶ አደሩ ዘር በተሻለ መልኩ እንዲቀርብለት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።
ማሻሻያው ኢትዮጵያ "የመጠባበቂያ ዘር ስርዓት" እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የዘር ለቀቃና ምዝገባ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር መደምደሚያው ነቅንቄ ለኢዜአ እንዳሉት፤አዋጁ የዝርያ ለቀቃ ስርዓት፣ ምዝገባና ዝርያ ማሻሻያ አሰራሮችና ሕጎችን በተሻለ ደረጃ ያካተተ ነው ።
በውጭ ሀገር የተሰራ የዝርያ ባህሪ ልየታና ቅበላን ጨምሮ አዳዲስ የዘር ብዜት እንዲሁም፣ የጥራትና ቁጥጥር ስራ በመንግስት፣ በግሉ ዘርፍና በአምራች አርሶ አደሮች ጭምር እንዲከናወን የሚያስችል አሰራራ መያዙን አመልክተዋል።
ከዘር ቁጥጥር አንጻርም ከመንግስት ውጭ ሶስተኛ ወገን በሕጋዊ መንገድ ተደራጅቶ እውቅና ካገኘ መቆጠጣር የሚችልበት አማረጭ መያዙንም ገልጸዋል።
''ከዚህ በፊት የአዳቃይ ዘር ወይም 'እናት ዘር' ቁጥጥር አይደረግበትም ነበር'' ያሉት ዶክተር መደምደሚያው በሚሻሻለው አዋጅ ቁጥጥር እንዲደረግበት በአዲስ መልክ ተኳቷል ብለዋል።
ነባሩ አዋጅ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች የዘር እጥረት ሲከሰት የድንገተኛ ዘር ግዥ ተብሎ ከገበያ መግዛት እንደሚቻል ደንግጓል።
እንደ ከፍተኛ ባለሙያው ገለጻ፤ በሚሻሻለው አዋጅ ኢትዮጵያ የመጠባበቂያ ዘር የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖራት የሚያስችል ነው።
በነባሩ አዋጅ የዝርያ ብቃት ሙከራ በግብርና ሚኒስቴር ብቻ ሲደረግ እንደነበርና በማሻሻያው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ አመልካቹና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ አማራጭ የሰጠ ይሰጣል ብለዋል።
በውጭ ሀገራት የተሻለ ምርጥ የሚሰጡ ዝርያዎችን የማላመድና ከኢትዮጵያ የአየር ጠባይ ጋር ተስማሚነት ካላቸው የሙከራ ስራ እንዲሰራባቸው እንደሚፈቀድም ነው ባለሙያው ያብራሩት።
በአጠቃላይ የአዋጁ ማሻሻያ ዘርን በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን 'የመጠባበቂያ ዘር ስርዓት' ለማበጀት ጭምር እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የግብርና እንቨስመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ በበኩላቸው "በዘር ላይ የሚደረገው የዝርያ ማሻሻያና ቴክኖሎጂ ምርትና ምርታማነትን በ30 በመቶ የሚያሳድግ ነው" ብለዋል።
በተለይ ትላልቅ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዘር ብዜትና የኮንትራት ስምምነት እርሻ መሰማራት ሲፈልጉ ከሚጠይቁት መካከል የዘር ማሻሻያ ሕግ መሆኑን አንስተዋል።
ማሻሻያው ለዚህም አመች የሆነ አሰራር የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው አዋጁን በግብዓት ለማዳበር ከባለድርሻ አካላት ጀምሮ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።