ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን በክህሎትና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ እንደሚጠናከር ተገለጸ

ጋምቤላ፣ የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን በክህሎትና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በክልሉ በአነስተኛና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለተሰማሩ ከ1 ሺህ 400 በላይ አንቀሳቃሾች ለ4ኛ ዙር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ስልጠናውን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገትና የብልጽግና ጉዞ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የጎላ ፋይዳ አላቸው።

የኢንተርፕራይዝ ልማቱን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚቻለው በእውቀትና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ መስራት ሲቻል ነው ብለዋል።

በክልሉ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ሊውል የሚችል ሰፊ የውሃ፣ የመሬት፣ የማዕድን፣ የእንስሳትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በመሆኑም የኢንተርፕራይዝ ልማቱን በእውቀትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ በክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት በመለወጥ የታለመውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲፋጠን የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በዕለቱ የተጀመረው ስልጠና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን አቅም በማጎልበት በተሻለ መልኩ ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትየጵያ ልማት ባንክ በክልሉ በዘርፉ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን አቅም በማጎልበትና የሊዝ ፋይናንስ ብድር አገልግሎት በመስጠት ጭምር እያሳየ ላለው ድጋፍና የልማት አጋርነት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አባተ በበኩላቸው ባንኩ በክልሉ በኢንተርፕራይዝ ልማት የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን አቅም በማጎልበትና የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት በመስጠት ዘርፉን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ባንኩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ በክልሉ ከ156 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ እስከ ግማሽ በጀት ዓመቱ ባለው ጊዜ 91 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል።

ባንኩ በክልሉ በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 600 ለሚሆኑ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና ለመስጠት ምዝገባ ማካሄዱንና በዛሬው እለት ለ1 ሺህ 400 አንቀሳቃሾች ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሚኖራቸው የአምስት ቀናት ቆይታ በቢዝነስ እቅድ ዝግጅት፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በግብይትና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም