በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶና ሽኝቱ የተቀናጀና የአገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ የተከናወነ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶና ሽኝቱ የተቀናጀና የአገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ የተከናወነ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የካቲት 14/2015 (ኢዜአ) በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶና ሽኝቱ የተቀናጀና የአገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ የተከናወነ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ገለጹ።
የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
የጉባዔውን ሂደት ስኬታማ ለማድረግ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ እስከ ሽኝት የነበረውን አጠቃላይ ክንውን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመግለጫቸው ከጉባዔው ውጤታማነት ባለፈ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ውስጣዊ ችግር ወጥታ የተሳካ ሁነት በማዘጋጀት እንግዳ የመቀበል አቅምና ብቃቷን በተግባር ያሳየችበት ነበር ብለዋል።
በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በአድናቆት የተነሳበት፣ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አማራጭ በተግባር የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ የተወሳበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ተሞክሮ በ2063 የአፍሪካ የልማት አጀንዳ ውስጥ አንዱ በሆነው የጥይት ድምፅ የማይሰማበት አፍሪካን ዕውን የማድረግ ግብ ማሳያ መሆኑ መወሳቱንም ጠቅሰዋል።
በጉባዔው ኢትዮጵያ በተለያዩ የሕብረቱ ተቋማት አባልነት ጉዳይ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከልና በኔፓድ የአመራር አባልነት እንዲሁም በሌሎች ኮሚቴዎች ውስጥ በአባልነት መመረጧን ገልጸዋል።
እነዚህ ተሳትፎዎችም ኢትዮጵያ ድምጿን ለማሰማትና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ማፋጠን በተመለከተ የሸቀጦች ንግድ ዝርዝር ጉዳይ የተገመገመበት እና ውይይት የተደረገበት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ የንግድ ማስተሳሰር አስፈላጊነት በአፅንኦት የተገለጸበት እና ኢትዮጵያ 90 በመቶ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀች በመሆኑና፤ የሀገራት ትብብር ውሳኔ የተላለፈበት ስብሰባ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ በርካታ ጠቃሚ የሁለትዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ቆይታ የኢኮኖሚ እምርታ ያሳየችበትና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ጥረት የተደረገበት እንደነበርም አስታውሰዋል።
በመሪዎቹ ጉባዔ ኢትዮጵያ ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ያሳየችበትና በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይሰራጩ የነበሩ የተዛቡ ዘገባዎች ትክክለኛ መልክ የያዙበት ነበር ብለዋል።
በቀጣይ ሐምሌ ወር የሚደረጉ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባዎችም በአዲስ አበባ እንዲደረጉ ውሳኔ መተላለፉንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው፤ የመሪዎች ጉባዔ በጸጥታው ዘርፍ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በትብብር መሰራቱንና በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የጋራ የፀጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይል ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠርና በአንድ ዕዝ እንዲመራ በማድረግ የተሳካ ሥራ መሰራቱንም አስታውሰዋል።
እንግዶችን ከቦሌ ኤርፖርት በመቀበል በጉባዔው ሲንቀሳቀሱና አጠቃላይ በቆይታቸው የጸጥታ ጥበቃውና የሕብረተሰቡ መስተንግዶ አስደሳች እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ለጉባዔው በስኬት መጠናቀቅ አጠቃላይ የከተማው ነዋሪ እና የጸጥታ ኃይሉ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።