የወተት ምርትን ጥራትና ጤንነት አረጋግጦ ለመጠቀም በፖሊሲ የተደገፈ አዲስ አሰራር መተግበር እንደሚገባ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የወተት ምርትን ጥራትና ጤንነት አረጋግጦ ለመጠቀም በፖሊሲ የተደገፈ አዲስ አሰራር መተግበር እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 14/2015 በኢትዮጵያ የወተት ምርት ጥራትና ጤንነቱ ተረጋግጦ ጥቅም ላይ እንዲውል በፖሊሲ የተደገፈ አዲስ የአሰራር ስርዓት መተግበር እንደሚገባ በጥናት አመለከተ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በወተት ምርት ጥራትና ደህንነት ዙሪያ ላለፉት አራት ዓመታት ያካሄደውን የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡
የወተት ምርት ጥራት መጓደል ምክንያቶችን ለይቶ ማውጣት ላይ ያለመው ጥናት በአማራ፣ ኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የተካሄደ ነው፡፡
የጥናቱ መሪ ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ እንዳሉት፤ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ 2019 ጀምሮ የወተት አምራች ገበሬዎችን፣ አቅራቢዎችን፣ ሻጮችንና አቀናባሪዎችን ያካተተ የመስክ ምልከታና የቤተ- ሙከራ ጥናት ተድርጓል፡፡
በዚህም ወተት ተመርቶ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ ባለው ሂደት የምርቱን ጥራትና ደህንነት የሚቀንሱ ሁነቶች እንዳሉ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
የወተት የማሰባሰብና የማጓጓዝ ሂደት ምቹ አለመሆን፣ የፋብሪካ ማምረቻ ክፍሎች ንጽህና ጉድለት፣ የምርት ክምችትና አስተሻሸግ ጥራት ጉድለት በጥናቱ የተለዩ መሆናቸውን ጠቁመው የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ምርቶች ጥራትና ደህንነት ከደረጃ በታች ሆኖ በመገኘቱ በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
ከአምራች ገበሬዎች እስከ ተጠቃሚው ያለውን ሰንሰለት ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተል በማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ወተት ማምረት ለነገ የማይባል ስራ ያሉት ዶክተር አሻግሬ መንግስት ለዘርፉ ተዋናዮች ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ በፖሊሲ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመተግበር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አለበት በማለትም አመልክተዋል፡፡
የወተት ምርት ለስራ እድል ፈጠራና ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የቀንድ ከብት ብዛት አኳያ የምታገኘው የወተትና የወተት ተዋዕጾ ምርት ከአገር ፍጆታ የዘለለ አይደለም በማለት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት የወተት ምርታማነት፣ ጥራትና ደህንነት ለማሻሻል ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡