የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለኢኮኖሚው ያለውን ግዙፍ አስተዋጸኦ በመገንዘብ በዘርፉ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል- ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለኢኮኖሚው ያለውን ግዙፍ አስተዋጸኦ በመገንዘብ በዘርፉ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል- ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል
የካቲት 14/2015(ኢዜአ) የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ከራስ አልፎ ለአገር የሚጠቅም የልማት ዘርፍ መሆኑን በመገንዘብ በዘርፉ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አራተኛው ዙር የአነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ተጀምሯል።
በዚህ የሥልጠና መርሃ-ግብር 435 ሺህ ሰልጣኞች በሦስት ዙሮች ተከፋፍለው የሚሰለጥኑ ሲሆን በዛሬው እለት በ57 ከተሞች በሚገኙ 95 ማዕከላት 112 ሺህ የሚሆኑት ሥልጠና ጀምረዋል።
በሥልጠናው የመክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰዎች ሰርተው የሚያተርፉባቸው ተቋማት መሆናቸውን በአግባቡ ተገንዝቦ ወደ ዘርፉ የመሰማራት ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል።
የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማም በክህሎትና አመለካከት ሰልጣኞችን በመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ የዓለም አገራት የኢኮኖሚ እድገት መሰረታቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ለኢትዮጵያም ተመሳሳይ ጥቅም እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት፣ የዘርፉ ተዋናዮችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ለስኬታማነቱ በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል ከመፍጠርም ያለፈ አገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የዘርፉ ጠቀሜታ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ሥራም ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ለዘርፉ ስኬታማነት ለኢንተርፕራይዞች የመሥሪያ ቦታ ከማመቻቸት ባለፈ እገዛና ድጋፍ በማድረግ ጭምር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች አዋጭ በሆኑ የልማት መስኮች በመሰማራት ከራሳቸው አልፈው የአገሪቷን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሥልጠና ዋነኛ ዓላማው የንግድ ሥራ ዕቅድ አዘገጃጀትና ርዕይ ቀረፃ መሆኑን አንስተው የቢዝነስ ሥራ አመራር፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የገበያ ፍለጋና የሒሳብ አስተዳደርም የስልጠናው አካል መሆኑን አመልክተዋል።