ቀጥታ፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን የሚለወጡበት የሥራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ሚዛን አማን፣ የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) --የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን የሚለውጡበት የሥራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

ሀገር አቀፍ የልማት ባንክ 4ኛ ዙር የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና በክልሉ ቦንጋ እና ሚዛን አማን የስልጠና ማዕከል ተጀምሯል።

በቦንጋ የስልጠና ማዕከል በመገኘት ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት ክልሉ ለዜጎች ምቹና ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር የሚችል አቅም አለው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቡና፣ ፍራፍሬና የሻይ ምርትን ጨምሮ በሌሎች ቅመማ ቅመሞች እንዲሁም በማዕድን ልማትና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

በተለይ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ቡናና ሌሎች የኢኮኖሚ ምንጮችን የያዘ በመሆኑ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።

''ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ከሰው ኃይል ጋር በማስተሳሰር መስራት ከተቻለ የምናስበውን እድገት ማምጣትና የዜጎችን ህይዎት መቀየር እንችላለን'' ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ ፍላጎትና ተነሳሽነት ያላቸውን ወጣቶችና የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን የሥራ ክህሎት በስልጠና በመሙላት ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

የ4ኛ ዙር ሰልጣኞች ከስልጠናው የሚያገኙትን የሥራ ክህሎት ተጠቅመው በክልሉ ባሉ ሰፊ የሥራ መስኮች ቢሰማሩ ከራስ አልፈው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህ ስልጠና ውጤታማ እንዲሆን ክልሉ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣ ዶክተር ነጋሽ አረጋግጠዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች በዛብህ በበኩላቸው ስልጠናው ወጣቶች በዕውቀት ላይ ተመስረተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በርከት እንዲሉ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኦልያድ ቦቶሬ በሚዛን እና ቴፒ ከተሞች ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችና የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ለስልጠናው መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ቀድሞ የተመዘገቡ ከ750 በላይ ሰልጣኞች ከሚዛን እና ቴፒ ከተሞች በሚዛን የስልጠና ማዕከል ስልጠና መውሰድ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 18 ቀን 2015 ዓም ድረስ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም