ኢንተርፕራይዞች የተፈጥሮ ሃብትን ለኢኮኖሚው ግንባታ እንዲውል መስራት ይጠበቅባቸዋል- የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞች የተፈጥሮ ሃብትን ለኢኮኖሚው ግንባታ እንዲውል መስራት ይጠበቅባቸዋል- የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ
አሶሳ (ኢዜአ) የካቲት 14 ቀን 2015 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጥሮን ሀብትን በማልማት ለኢኮኖሚ ግንባታ እንዲውል መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች በሊዝ ፋይናንስንግ አገልግሎት ዘርፍ በአሶሳ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ስልጠናውን የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸሪፍ ሃጂአኑር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል ሰፊ የሆነ ለም መሬትና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የቱሪዝም መስህብ ሥፍራዎችም በክልሉ በስፋት እንደሚገኙ ጠቁመው፤ የተፈጥሮ ሀብቱን ለማልማት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በፍጥነት በማብቃት ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ሰልጣኞቹ የሚያገኙትን እውቀት በአግባቡ ተጠቅመው ሀብቱን በማልማት ለክልሉ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው አሳስበዋል።
ሰልጣኞች ወደ ሥራ እንዲገቡ ጽህፈት ቤቱ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአሶሳ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቤተማርያም ሰለሞን በበኩላቸው፤ስልጠናው ሀገር አቀፍ መሆኑን ጠቁመው፤ አሶሳና ግልገልበለስ ከተሞችን ጨምሮ 1 ሺህ 949 ሰልጣኞች ስልጠናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ባንኩ ከስልጠናው በኋላ ወደ ሥራ ለሚገቡ ሰልጣኞች በፕሮጀክት ፋይናንሲንግና በሊዝ ፋይናንስ የብድር ገንዘብና የተለያዩ ድጋፎች ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና የንግድ ሥራ አዘገጃጀትና ራዕይ ቀረጻን ጨምሮ የሥራ ፈጠራን የሚያጎለብቱ ንድፈ ሃሳብ በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።