“ፍቅር እስከ መቃብር” መፅሐፍን ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ቀይሮ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
“ፍቅር እስከ መቃብር” መፅሐፍን ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ቀይሮ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 14/2015 “ፍቅር እስከ መቃብር” መፅሐፍን በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለተመልካች ለማቅረብ ኢቢሲና ሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ የመፅሐፉን ታሪካዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ ወደ ቴሌቭዝን ድራማ ለመቀየርና ለተመልካች ለማቅረብ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት በክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ የተደረሰውና ዘመን ተሻጋሪው “ፍቅር እስከ መቃብር” የልቦለድ መፅሐፍ በዘመኑ የነበሩትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖያዊና ማህበራዊ ገፅታዎች በግልፅ የሚያሳይ ነው።
በወቅቱ የነበረውን የማህበረሰቡን አኗኗ፣ ወግና ባህል ከማሳወቁም በላይ በጊዜው የነበረውን ስርዓት በጥልቀት የሚፈትሽና የሚተች እንዲሁም ተራማጅ እሳቤዎችን የሚያንጽባርቅ ነው በማለት ጠቅሰዋል።
መፅሐፉ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በታዋቂው የኪነጥበብ ሰው ወጋየሁ ንጋቱ ተተርኮ በብዙ ኢትዮጵያውያን ጆሮና ልብ ውስጥ መድረስ ችሏል በማለት አስታውሰው ኢቢሲ ይህንን ድንቅ መፅሐፍ በድምፅ ከመተረክ ባሻገር የህዝቡን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ስምመነቱን መፈጸሙን ተናግረዋል።
ለዛውን በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ ወደ ቴሌቪዥን ድራማነት ተቀይሮ ለተመልካቾች ለማድረስ በዛሬው ዕለት ከተባባሪ አካል ጋር ስምምነት መፈጸሙን ነው የተናገሩት፡፡
የሰውመሆን ይስማው ፊልም ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማው በበኩሉ፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ድንቅ መፅሐፍ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በቴሌቪዥን ድራማ ፕሮዳክሽን ለማዘጋጀት ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጿል።
መፅሐፉ ወደ ተካታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሲቀየርም የዚህ ዘመን ትውልድ ካለፈው ትውልድ በማገናኘት ትምህርት የሚቀስምበትን ዕድል ይዞ መምጣቱን አመልክቷል፡፡