ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ44 ዩኒቨርሲቲዎች የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቶችን ሊከፈት ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 14 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ44 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶችን ለማቋቋም ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

በትግበራ ሂደት ምዕራፉ የምክክር አጀንዳ ልየታ መርሃ ግብርን መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ እንደሚያከናውንም ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

መንግስት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ መግባባትን ለመፍጠር ምክክርን የሚያመቻች ኮሚሽን ለማቋቋም ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም አዋጅ ቁጥር 1265/ 2014ን ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ማፅደቁ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክሩን የሚያሳልጡና የኮሚሽኑን ሥራ የሚከውኑ 11 ኮሚሽነሮችን የሾመው የዛሬ ዓመት የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም መሆኑም ይታወሳል።

ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ የቅድም ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የትግበራ እንዲሁም ግምገማና ክትትል ምዕራፎችን ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በዚህም የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፎችን በአንጻራዊነት በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቱን ነው የተናገሩት።

በቀዳሚዎቹ ምዕራፎች ውስጥ የኮሚሽኑን ዓላማ የማስገንዘብ፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መሰብሰብ፣ ስትራቴጂዎችንና መመሪያዎችን የማዘጋጀት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት የመሰብሰብ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች እና በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የቆየው የጥላቻ የፖለቲካ ባህል ኮሚሽኑን ቢፈትኑትም ዓላማውን በማስገንዘብና ያቀደውን በማከናወን ረገድ የተሻለ ሥራ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

በኮሚሽኑ ወደ ትግበራ ለማምራት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ48 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አሁን ላይ በ44ቱ የኮሚሽኑን ሥራዎች የሚያሳልጡ ጽሕፈት ቤቶችን ለማቋቋም ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።

ጽሕፈት ቤቶቹን ለመክፈት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲዎችን ምቹነት በማረጋገጥ የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶችን ለማቋቋም ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በየፅህፈት ቤቶቹ በቂ የሰው ኃይል ለመመደብ እንደ አካባቢው ሁኔታ ከህዝባዊ ተቀባይነት፣ ከቋንቋ፣ ከባህልና ሌሎችንም መስፈርቶች በማስቀመጥ ምስጉን የሆኑ ባለሙያዎችን ለመቅጠር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰው ኃይል ቅጥር እንደተጠናቀቀም ሙሉ ጽሕፈት ቤቶች የመጋቢት ወር ከመጠናቀቁ በፊት እንደሚከፈቱ የጠቆሙት ዶክተር ዮናስ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡበት ምክንያትም "ከገለልተኛነታቸውና ትንሿ ኢትዮጵያ" ከመሆናቸው አኳያ መሆኑን አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎችን ከነበረው ሁኔታ አንጻር እስካሁን ማወያየትና መጎብኘት እንዳልተቻለ ጠቅሰው፤ በቀጣይ ሥራ ሲጀምሩ ጽሕፈት ቤቶች እንደሚከፈቱ ጠቁመዋል።

ዶክተር ዮናስ አክለውም የትግበራ ሂደቱ ለዋናው ሀገራዊ ምክክር መንደርደሪያ የሚሆኑ የአጀንዳ ልየታ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸው፤ ይህም መጋቢት መጨረሻ ላይ እንደሚጀመር ነው የጠቆሙት።

ሀገራዊ ምክክሩ ከታች ከህብረተሰቡ ወደ ላይኛው የመንግስት መዋቅር የሚደርስ ሰንሰለት እንደሚኖረው ያነሱት ኮሚሽነሩ፤ አጀንዳ ልየታውም ከማህብረሰቡ ጋር በመወያየት እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር አንደኛው ዓላማው ነው።

የመነጋገር የፖለቲካ ባህልን ለማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት በጋራ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ሽግግር በማምጣት ልማትን ማፋጠንም የምክክሩ ግቦች መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም