ቀጥታ፡

የመጀመሪያው አህጉር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት የምክክር ጉባኤ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 14 ቀን 2015 የመጀመሪያው አህጉር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት የምክክር ጉባኤ በመጪው ሳምንት የካቲት 21/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን አህጉር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ጉባኤው በመጪው ሳምንት የካቲት 21/2015 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር በመተባበር በሚያዘጋጀው በዚህ መድረክ በአህጉሪቱ ለሚስተዋሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ይመክራል ብለዋል።

ሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ መርህ እና እሴት እንዲጠበቅ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመንግስታት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ምክረ ሃሳብ እንደሚቀርብም ገልጸዋል።

ሃይማኖቶች ስ ለሰላም፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ብዝኃነት፣ ስለተፈጥሮ ሃብት አያያዝና ጥበቃ፣ ስለ ዘላቂ ልማትና ነፃነት በአጽንኦት እንዲያስተምሩ የልምድ ልውውጥ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ጉባኤው በቀጣይነት በአፍሪካ ኅብረት በኮሚሽን ደረጃ በየዓመቱ እንዲካሄድ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

በሃይማኖቶች መካከል ትብብርን፣ የአማኞችን አብሮነት፣ የውይይት ባህልን ማጠናከር እና የአፍሪካ ሕብረት የቡድን 20 አባል ለመሆን የጀመረውን ጥረት በምክረ ሃሳብ ማገዝ የጉባኤው ዓላማዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

ቀሲስ ታጋይ አክለውም የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ መንፈሳዊ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጨምሮ 300 ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሏል።

በቀጣይ ሳምንት የሚካሄደው አህጉር አቀፍ ሃይማኖት ተቋማት የምክክር ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ባህልና ሥርዓት አስተናግዶ መሸኘት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም