ቀጥታ፡

ከመቶ ሺ በላይ ሰልጣኞች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ተጀመረ

የካቲት 14/2015 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ከአንድ መቶ ሺ በላይ ሰልጣኞች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ተጀመረ።

በማስጀመሪያ መርሐግብሩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ፣የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ስልጠናው በሶስት ዙሮች የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ስልጠና በ57 ከተሞች በሚገኙ 95 ማእከላት እንደሚጀመርና በስልጠናው 112 ሺህ ሠልጣኞች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።

ስልጠናው በዋናነት የንግድ ስራ እቅድ አዘገጃጀትና ርእይ ቀረጻ፤ የቢዝነስ ስራ አመራር, የሰው ሃብት ፤ የገበያ ፍለጋና ፤ የሂሳብ አስተዳደር እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአዲስ አበባ ደረጃ ከ 14 ሺህ በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ተናግረው የአነስተኛ እና መካከለኛ አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞች በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ስልጠናው ይህንን አቅም በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጠቆም ሰልጣኞች ስልጠናውን በከፍተኛ ትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው በበኩላቸው በአራተኛው ዙር ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ ጉዳዮች መካተታቸውን ተናግረው መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት ለባንኩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባንኩን ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።

ባንኩ በሰጠው ሶስት ዙር ስልጠና እስካሁን 33 ሺህ ሰዎች ማሰልጠኑንና በአራተኛው ዙር ስልጠና ለመካፈል 435 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም