ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ለተፈናቃይ ወገኖች 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ተደረገ

ደብረ ብርሃን ( ኢዜአ ) የካቲት 13/2015 በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ተደረገ ።

ድጋፉ የተደረገው በዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን ነው።

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ድባቤ ዛሬ በተደረገው የድጋፍ ርክክብ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት በከተማው 26 ሺህ ተፈናቃይ ወገኖች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።

ከመንግስት የተለያዩ ረጅ ድርጅቶችን በማስተባበር ለተፈናቃይ ወገኖች የእለት ምግብ እንዲደርስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል ።

ተፈናቃይ ወገኖች ወደቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ በመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በባለሃብቶችና በማህበረሰቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን ፕሬዚዳንት አቶ እንዳልካቸው ዘውዴ በበኩላቸው ''ሁሉም እጆች ለኢትዮጵያ በሚል'' መሪ ሃሳብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያንን በማስተባበር ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል ።

ድጋፉ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 900 ኩንታል ዱቄትና 2 ሺህ 500 ሊትር የምግብ ዘይት መሆኑን አመልክተዋል።

ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀደመ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም