ኢትዮጵያ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች- የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች- የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2015 ኢትዮጵያ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የስንዴ እና በቆሎ ማሻሻያ ማዕከል ከአረንጓዴ ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር የግብርና ሜካናይዜሽን ለማሳደግ የሚረዳ ዓለም አቀፍ የስራ ቡድን አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ከየካቲት 13 እስከ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት በሚካሄደው የአውደ ጥናት የምክክር መድረክም ከግብርና ሚኒስቴር እና ከተለያዩ አገራት የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የሜካናይዜሽን መሪ ስራ አስፈፃሚው በረከት ፎርሲዶ፤ ግብርና የኢትዮጵያ ወሳኝ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
መንግስት የሰብል እና እንስሳት ምርታማነትን በማዘመን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ግብርናው ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ውስጥ 32 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንደሚሸፍን ተናግረዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ከሚተዳደሩ ዜጎች መካከል በርካቶች በሰብል ልማት እንደሚሳተፉም ነው ያብራሩት፡፡
አሁን ላይ የግብርናውን ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የሜካናይዜሽን ስራ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን ድህነትን ለመቅረፍ በምታከናውነው ስራ ውስጥ የልማት አጋር ድርጅቶችን ትብብር እንደምትሻም ጠቁመዋል፡፡
ከበለጸጉ አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘቸውን ራዕይ እውን ለማድረግም ያደጉ አገራትን የተሻለ ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግም እንዲሁ፡፡
በዓለም አቀፉ የበቆሎ እና የስንዴ ማሻሻያ ማዕከል የግብርና ሜካናይዜሽን ባለሙያው ራቤ ያህያህ በበኩላቸው አውደ ጥናቱም የግብርና ሜካናይዜሽን እድገትን ማሳለጥ የሚያስችል የልምድ እና የክህሎት ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱ በግብርና ምርታማነት እሴት ሰንሰለት የተሻለ ልምድ ያላቸው አገራት ለሌሎች ልምድ የሚያካፍሉበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአረንጓዴ ፈጠራ ማዕከል (ጂ.ኢ ሲ) ምክትል የፕሮግራም ኃላፊው ክርስቲን ሾትኮህ ናቸው፡፡