ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አከናውናለች - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2015 ኢትዮጵያ ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማከናወኗን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ "የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲመክር ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል።

በጉባኤው የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ የህብረቱን የሊቀ-መንበርነት ቦታ ከሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ተረክበዋል።

ሊቀ-መንበሩ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ለማፋጠን እንዲሁም በአህጉሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲረግቡ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩባቸው ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ለሁለት ዓመታት የነበረው ግጭት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሰላም መፈታቱን በመግለፅ ይህም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ ኢትዮጵያ በተግባር እየሰራች መሆኗን ያሳየ ነው ብለዋል።

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በአንድነት መስራት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ከአፍሪካ አገራት መሪዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ 42ኛውን የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባና 36ኛውን የመሪዎች ጉባኤ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በስኬት አስተናገዳለች።

ከጉባኤው ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጉባኤው ከነበራቸው ጉልህ ተሳትፎ ባሻገር፤ ከአፍሪካ መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ያነሱት።

በዚህም ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲ ትልቅ ስኬት እንዳስመዘገበች በመግለፅ።

አምባሳደር ብርቱካን አክለውም 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የቆየ የእንግዳ ተቀባይነቱን በማሳየት ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

በዚህም መሪዎቹ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሀገራቸው፤ አዲስ አበባም የአፍሪካውያን መዲና መሆኗን በተግባር እንዲመሰክሩ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ህዝቡ፣ የፀጥታና ደህንነት መዋቅሩ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች ላበረከቱት ጉልህ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በ42ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት እና በ36ኛው የመሪዎች ጉባኤ ሲሳተፉ የቆዩ አፍሪካውያን መሪዎች ወደ የሀገራቸው ተመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም