አፍሪካ ያላትን የኃይል አማራጭ አሟጣ መጠቀም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ነድፋ እየሰራች መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ያላትን የኃይል አማራጭ አሟጣ መጠቀም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ነድፋ እየሰራች መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አስታወቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 አፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድቷን ለማረጋገጥ ያላትን የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ መጠቀም የሚያስችላት ፍኖተ ካርታ ነድፋ እየሰራች መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አስታወቀ።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ምክትል ኮሚሾነር ዶክተር አቡ ዘይድ አማን በአፍሪካ የሃይል ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አፍሪካ ተመጣጣኝና ተደራሽ የኃይል አቅርቦት የትራንስፖርትና ዲጂታላይዜሽን መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
ላለፉት ዓመታት በነበሩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ችገሮችና ፖለቲካዊ ክስተት ምክንያት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ክፉኛ መጎዳቱንም አስታውሰዋል።
በዚህ ጫና ውስጥ ሆናም ችግሩን ለመቅረፍ በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች እንደ አህጉር መልካም ውጤቶች እንደተመዘገቡ ጠቅሰዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዘርፍ አፍሪካ ከፍተኛ እጥረት እንዳለባት ገልፀው፤ ችግሩን ሁሉም ሀገራት የኃይል አማራጫቸውን አሟጠው የሚጠቀሙበት ስትራቴጂ እየተመራች መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የግሪን ሀይድሮጂ የኃይል አማራጭን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን እና የአፍሪካ ትልቅ ተግዳሮት የሆነውን የአቪየሽን ነዳጅ የአቅርቦት ክፍተት በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት አፍሪካ አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ እንዲኖርም ፍኖተ ካርታ መቀረፁን አስታውሰው፣ ይህም በዓለም ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ለአፍሪካዊያን ትስስር ቁልፍ ጉዳይ ነው ባሉት የትራንስፖርት ዘርፍም በ35 ሀገራት የአንድ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ይህን ጅምር በባቡርና በሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ተደራሽ በማድረግ አፍሪካን የማስተሳሰር ስራዎች እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።
አፍሪካ በ2022 የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ማዘጋጀቷ ሁሉም ዘርፎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ መልካም ዕድል የፈጠረና የተጎዳውን ኢኮኖሚ መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እንዲከናወኑ አጋጣሚወን የፈጠረ እንደነበር አውስተዋል።
በዲጂታላይዜሽን በኩልም በሁለም መስክ አፍሪካ አቀፍ የጋራ ገበያ እንዲፋጠን የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነት በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ዲጂታል መታወቂያ ዝግጅትንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የዲጂታላይዜሽን ትግበራው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግንም ይጠይቃል ብለዋል።
የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ቻይናን ጨምሮ አህጉሪቷን በሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሚያከናውኑ አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልፀዋል።