ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አህጉራዊ አጀንዳ በማድረግ ሊተገብሩት ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 አፍሪካውያን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አህጉራዊ አጀንዳ በማድረግ ሊተገብሩት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የአፍሪካ አመራር ልኅቀት አካዳሚ ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም ዛሬ አካሂዷል። 

በፎረሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል። 

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና እንቅስቃሴን መልሶ ማነቃቃት ላይ ባተኮረው መድረክ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዋን አቅርባለች። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ባለፉት አራት ዓመታት በመተግበርና ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክሏል።

በመርሃ ግብሩ የምግብ ዋስትናን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሰፊ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ አህጉራዊ አጀንዳ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱንም ጠቅሰዋል።

የአረንጓዴ ልማት ለሁሉም የሰው ልጆች የሚጠቅም በመሆኑ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ስራዎች በሌሎችም አገሮች ቢቀጥሉ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አፍሪካውያን ጫና እየፈጠረባቸው ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ከመቋቋም ባለፈ ድህነትን ለማስወገድ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አህጉራዊ አጀንዳ በማድረግ ሊተገብሩት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የተራቆተ መልክዓ ምድሯን በአረንጓዴ እየሸፈነች ስለመሆኗ አንስተዋል። 

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ የሚያስተሳስሯት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዳይደርቁ በተፋሰሱ የደን ማልማት ስራ እያከናወነች መሆኑን ነው ያብራሩት። 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዓለም አቀፋዊውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም አፍሪካውያን በአንድነት መነሳት እንዳለባቸው የሚያመላክት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመከተል ፓን አፍርካኒዝምን በአረንጓዴ ልማት መድገም ይገባናል ነው ያሉት። 

የፎረሙ ተሳታፊ የነበሩት የአገራት መሪዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ከመድረኩ መጠናቀቅ በኋላ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም