ቀጥታ፡

ቅርንጫፍ ማህበሩ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው

ጂንካ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአርሶ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ማህበሩ በደቡብ አሪ ወረዳ ዶርዶራ፣ ሜፀር እና ጎይዳመር በተባሉ አካባቢዎች በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሦስት የውሃ ተቋማትን በመጠገን ለአገልግሎት አብቅቷል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ምልከታ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ማህበሩ ከተለያዩ አካላት ባገኘው 10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እያከናወነ ነው።

በቅርቡም በ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ በባካ ዳውላ አሪ ወረዳ በጸሐይ ሀይል የሚሰራ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋም ገንብቶ ለማህበረሰቡ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

በደቡብ አሪ ወረዳ ዶርዶራ፣ ሜፀር እና ጎይዳመር አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የተገነቡ ሦስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትም በብልሽት ምክንያት ለዓመታት አገልግሎት ባለመስጠታቸው ህብረተሰቡ ተቸግሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

ማህበሩ ከ850 ሺህ ብር በላይ በጀት በመመደብና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ አዲስ የመስመር ዝርጋታና የጥገና ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማከናወኑ የውሃ ተቋማቱ ዳግም አገልግሎት መስጠት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማቱ 650 አባዎራዎችን ከነቤተሰቦቻቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።

የደቡብ አሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከመንግስት ጎን ሆኖ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የወረዳው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 32 በመቶ መሆኑን ጠቁመው በመንግሥት በጀት፣ በማህበረሰቡ እና በአጋር ድርጅቶች ተሳትፎ በቀጣይ 10 ዓመታት ሽፋኑን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ አንግሲ በበኩላቸው በዞኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 36 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ሽፋኑን ወደ 37 ነጥብ 5 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ግንባታቸው ከሚጠናቀቁ ሰባት አነስተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት በተጨማሪ በማሌ፣ በበና ፀማይ እና በጂንካ ከተማ ትላልቅ የውሃ ተቋማት በግንባታ ላይ ናቸው።

የውሃ ተቋማቱ በመንግስት፣ በማህበረሰብ ተሳትፎ እና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በ576 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡ መሆኑንም አቶ አለማየሁ አስታውቀዋል።

"የውሃ ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የዞኑን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ50 በመቶ በላይ ያሳድጉታል" ሲሉ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም