የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት መቀየር ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት መቀየር ይገባል - ምሁራን
ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች አካባቢን እንዳይበክሉ ከማድረግ ባለፈ ወደ ሐብትነት በመቀየር ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
''ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት መቀየር'' በሚል መሪ ሐሳብ 2ኛው አቀር አቀፍ ጉባኤ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንሩት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በጉባኤው እንደገለጹት ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚወጡና በአግባቡ የማይወገዱ ተረፈ ምርቶች ዘርፈ ብዙ ጉዳት አላቸው።
ተረፈ ምርቶቹን በዘመናዊ መንገድ ማስወገድ ካልተቻለ አካባቢን ከመበከል ባለፈ ለሰው ልጆች የጤና ችግር መንስኤ መሆኑን ገልፀዋል።
ተረፈ ምርቶቹን ወደ ሐብትነት በመቀየር አካባቢን ከብክለትና ከሚያደርሱት የጎንዮሽ ጉዳት ከመታደግ ባለፈ ወደ ሐብትነት መቀየር ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ጥናትና ምርምር በማድረግ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት በመቀየር ጉዳታቸውን ከመከላከለ ባለፈ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ በመስራት በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዚህ ረገድ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሃብትነት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም /የዓሳ ቅርፊት/ የሚባለውን ተረፈ ምርት “ኮሊጅን” የሚባለውን የፕሮቲን ክፍሉን በማውጣት ወደ ሰውነት ቅባትነት መቀየር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ከዓሳ ተረፈ ምርት የሚሰራው ቅባት ለቆዳ ጤና ተፈላጊ መሆኑን በማረጋገጥ ይህንኑ ምርት ወደ ቢዝነስ የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።
በመሆኑም በቀጣይም ምሁራን ጥልቅ ምርምር በማድረግ ተረፈ ምርቶች ለኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ተባብረው መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
''ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት መቀየር'' የሚል መነሻ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር እምባለ መንግስቴ በበኩላቸው ተረፈ ምርቶችን ጥቅም ላይ ማዋል መቻል ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁሶችን በመተካት ኢኮኖሚያዊ ችግርን የሚያቃልል ነው ብለዋል።
ጊዜው የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የተስፋፋበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ መያዝና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብትነት በመቀየር ጉዳታቸውን ከመከላከል ባለፈ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻል በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ማፍራት ተገቢ እንደሆነም ገልፀዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ፋሽንና ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምርና ምርምር የሚያደርግ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ጉባኤው በኢንስቲትዩቱ መካሄዱም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሃብትነት ለመቀየር መነሳሳትንና አቅም ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።
በዚሁ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ፋሽንና ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው ጉባኤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የዘርፉ መምህራንና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።