ኢትዮጵያዊያን ለውጡን ለማስቀጠል በጋራ እንዲረባረቡ መንግሥት ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን ለውጡን ለማስቀጠል በጋራ እንዲረባረቡ መንግሥት ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 በኢህአዴግ 11ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና የሚቀመጡ አቅጣጫዎች ውጤታማ እንዲሁኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት ጥሪ አቀረበ። የድርጅቱ 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አመልክቷል። በአገሪቷ አሁን እየታየ ያለው የፖለቲካ መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን ህልውናዋን የታደገ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ጠቅሷል። ከማረሚያ ቤት የወጡ፣ ከትጥቅ ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱ እንዲሁም በውጭ አገር የነበሩ ተቃዋሚ ሃይሎች በኢህአዴግ ጉባኤ በመገኘት ሀሳባቸውን ማንጸባረቃቸው መንግስት የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰዳቸውን እርምጃዎች የሚያሳይ ነውም ብሏል። የመሪ ድርጅቶች ጉባኤዎች ሲካሄዱ ህዝቡ ያለ ምንም መሸማቀቅ የመሰለውን ሀሳብ ማንሳቱና መገናኛ ብዙሃንም ሀሳቦችን በነጻነት ማንሸራሸራቸው ተስፋ ሰጪ የለውጥ ክስተት እንደሆነም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል። በመሆኑም "በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ሲባል መሪው ድርጅት በጠቅላላ ጉባኤው ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተግባራዊነት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ እንዲረባረቡ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።" ብሏል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል። ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም. አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት በጋራ እንረባረብ! የመሪ ድርጅቱ -ኢህአዴግ- አባል ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤዎቻቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ "አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባዔ በብዙ መልኩ ሲታይ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ነው። አገራችን በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ በምትገኝበት እና በእስካሁኑ ሂደትም ጉልህ፣ መሰረታዊ እና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ላይ የተካሄደ በመሆኑ በእርግጥም ታሪካዊ ያደርገዋል። በተለይም አሁን የተፈጠረው ፖለቲካዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የአገራችንን ህልውና የታደገ በመሆኑ ከምንም በላይ የለውጡ ታላቅ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ያለበት አብይ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት በወሰዳቸው አበይት የለውጥ እርምጃዎች የተነሳ ከማረሚያ ቤት የወጡ፣ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ በህጋዊነት ከሚንቀሳቀሱት በተጨማሪ በውጭ አገራት ሆነው የተቃውሞ ፖለቲካ ሲያራምዱ የቆዩ ሃይሎች ሁሉ በጉባኤዎቹ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ እየተገኙ ሃሳባቸውን ሲያንጸባርቁና ምክራቸውን በይፋ ሲለግሱ የታዩበት ሂደት በእርግጥም የታላቅ ክንውን ውጤት መሆኑ አይዘነጋም። ጉባኤዎቹ በሚካሄዱበት ወቅት ሕዝብ ያለምንም መሸማቀቅ የመሰለውን ሃሳብ እየገለጸ ሚዲያዎቻችን የተለያዩ ሃሳቦችን በነጻነት ሲያንሸራሽሩ ማዬት ተስፋ ሰጪ የለውጥ ክስተት ነው። በውጭ አገራት ሆነው በሚያራምዱዋቸው የተለዩ ሃሳቦች የተነሳ ተዘግተው የነበሩ ሚዲያዎች እና ድረገፆች ዛሬ በመሪ ድርጅቱ እና በመንግሥት የስብሰባ አዳራሾች እየተገኙ ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮችን በነጻነት እየዘገቡ ያሉበትን ሁኔታ በአጽንኦት መመልከትም የጉባዔውን ታሪካዊነት ለመመስከር የሚያግዝ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ረገድ የራሳቸውን ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ህግጋትን በሕዝቡ፣ በምሁራን እና በባለሙያዎች አስተያየት እና ተሳትፎ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር የነበረባቸውን የጸጥታ እና የህግ አስከባሪ ተቋማትን የህዝብ አገልጋይ ለማድረግ ከአመራር እስከ አደረጃጀት እና አሰራር ማሻሻያ የዘለቀ የለውጥ ሥራ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት የተካሄደ ጉባዔ እንደመሆኑ መጠን ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል። ተወደደም፣ ተጠላም የአገራችን መጻኢ ዕድል በጎም ይሁን መጥፎ የሚወሰነው አሁን ባለው ትውልድ መሆኑን በጥልቀት መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን የብሔር እና የፖለቲካ ልዩነቶችን መሰረት አድርገው ከመቆራቆስ ወጥተው ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ሃብትና ጉልበታቸውን አስተባብረው ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለብልጽግና ለእኩልነት እና ለአንድነት በጋራ ለመስራት ከዚህ የተሻለ ዕድል አይኖራቸውም። የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ የሚያደናቅፉና አቅጣጫ የሚያስቱ ተግባራትን በጋራ ሆኖ በመግታት ለለውጥ ሂደቱ ያላቸውን አጋርነት በተግባር የሚያረጋግጡበት ወቅት መሆኑንም መገንዘብ ይገባል። ይህ አጓጊ እድል የተገኘው በዋዛ ሳይሆን በከፍተኛ መስዋዕትነት እንደመሆኑ መጠን ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ብዝሃነታችንን ያከበረ አገራዊ አንድነትን በማስቀደም፣ የአንዳችን ጉዳት የሌላችን ጉዳት መሆኑን አምኖ በመቀበል የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሁላችንንም አገራዊ ኃላፊነት መወጣት የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ሲባል መሪው ድርጅት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተግባራዊነት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ እንዲረባረቡ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።