ቀጥታ፡

የናጀሪያና ኢትዮጵያን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 የናጀሪያና ኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂኦፍሪይ ኦንያማ ገለጹ።

የናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂኦፍሪይ ኦንያማ፤ በአዲስ አበባ በተካሄደው በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ የህብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል ናቸው።

ከዚሁ ጉባኤ በተጓዳኝ የኢትዮጵያና ናይጀሪያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂኦፍሪይ ኦንያማ፤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም የኢትዮጵያና የናይጀሪያ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገሮች አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂኦፍሪይ ኦንያማ ተናግረዋል።

በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ የአየር ትራንስፖርትና ሌሎችም የትብብር መስኮች በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ናይጀሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በተለያዩ ዘርፎች ለማሳደግ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጀሪያ በማቋቋም ላይ ያለችውን ብሔራዊ አየር መንገድ እንዲያስተዳድር መመረጡ የጠንካራ ግንኙነቱ ማሳያ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የአህጉሪቱን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በአገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንና ሌሎች ግንኙነቶች ማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ የንግድ ልውውጥ ከአህጉሪቱ ውጭ እንደሚከናወን ገልጸው ይህም አፍሪካ እየገጠሟት ካሉ ችግሮች መካከል ይጠቀሳል ነው ያሉት።

ከምዕራባውያን ጥገኝነት በመላቀቅ የእርስ በእርስ ግንኙነትና ውህደትን በማጠናከር ለዜጎቿ የምትመች አፍሪካን እውን ማድረግ የጋራ ስራችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

አፍሪካ አምራች የሰው ሃይልና ያልተነካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አህጉር በመሆኗ በጋራ ከሰራን የምንሻውን እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም