ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሆኑ መዛግብትን በተገቢዉ መንገድ ማደራጀትና ያልተዛቡ ታሪኮችን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል-የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሆኑ መዛግብትን በተገቢዉ መንገድ ማደራጀትና ያልተዛቡ ታሪኮችን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል-የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት
ሆሳዕና (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 ቀዳሚ የመረጃ ምንጮች የሆኑ መዛግብትን በተገቢዉ መንገድ ማደራጀትና ያልተዛቡ ታሪኮችን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ በአብያተ መዛግብትና በአብያተ መፃህፍት አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።
ተቋሙ የንባብ ባህልን ለማጎልበት የሚያግዙ ከስድስት መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መፃህፍትን ለስምንት ትምህርት ቤቶችና በዱራሜ ከተማ ለሚገኘው የህዝብ ቤተ-መፃህፍት ድጋፍ ማበርከቱንም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት የአብያተ መፃህፍት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ተፈራ በውይይቱ ላይ እንዳሉት የተቋሙ ዋና ተልእኮ መረጃዎችን በማሰባሰብ ማደራጀት ነው።
የድንበር ስምምነቶችን ጨምሮ ለሀገር ማስረጃነት የሚያገለግሉ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ ሰነዶችን ከታዋቂ ግለሰቦችና ከመንግሥት ተቋማት ማሰባሰብ ላይ በትኩረት እየተወጣ ነው ብለዋል።
ትክክለኛ ታሪክ እንዲመዘገብ የመረጃ አያያዝና የታሪክ መዛባቶችን አስተካክሎ ለማስቀጠል የአሰናነድ ችግሮችን ማስጠበቅ ቁልፉ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተቋሙ የሀገሪቱን ታሪኮች በአግባቡ ሰንዶ በማስቀመጥ እውነታውን አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስቀጠልን ዓላማ በማንገብና የንባብ እሴቶችን ማጠናከር ላይ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ቀዳሚ የመረጃ ምንጮች የሆኑ መጻህፍትንና መዛግብትን በአግባቡ በማደራጀት ቀጣይ ትውልድ ያልተበረዘ ታሪክ ወራሽ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ተቋማት የሚስተዋሉ የመረጃ አያያዝ ችግሮችንና አሰራሮችን በማሻሻል ለተተኪው ትውልድ ትክክለኛ መረጃን ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በትክክለኛ መረጃ አያያዝ ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተግባራዊነት ለማጠናከርና መነሳሳትን ለመፍጠር የንባብ ሳምንት ማስጀመሪያዎቹ መሰረታዊ ዓላማ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህም የነበሩ እሴቶችን አስጠብቆ በማስቀጠል ይዘታቸውን ሳይለቁ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል ይጠበቃል ብለዋል።
የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ በበኩላቸው ቢሮዉ በህብረተሰቡ ዘንድ የንባብ ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ ስራዎችን ከተቋሙ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በክልሉ የሚገኙ ነባር እሴቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም እሴቶችን በመለየት እንዲጠበቁና በሰነድ ተጀራጅተዉ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክንያታዊ ዜጋን ለማፍራት ንባብ ባህል ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ በከምባታ ጠምባሮ ዞን የዱራሜ ሀምቦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህርት ወይዘሮ ራሄል ያዕቆብ ናቸው።
በመጻሀፍት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ዜጎችን በንባብ የማነቃቃት ስራ ማስጀመር መቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ለትምህርት ቤታቸው በተደረላቸው የመጻሐፍት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውነ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት አገልግሎት፣ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።