በየዘመኑ መለምለም ያለበት የኢትዮጵያ የአንድነት ተምሳሌት - ኢዜአ አማርኛ
በየዘመኑ መለምለም ያለበት የኢትዮጵያ የአንድነት ተምሳሌት
በቀደሰ ተክሌ (ኢዜአ)
የሰው ልጆች መኖሪያ የሆነቸው ዓለም በአንዲት ምድር ላይ የተወሰነች ናት። በምድራችን ደግሞ በብዙ አሉታዊና አዎንታዊ መንገድ መከፋፈል ይስተናገድባታል። በአህጉር ቅርጿን ከፋፍላ የጥቁር የነጭ፣ የቆላ የደጋ እያለች ድንበር ታበጃለች። ይህ ድንበር በመሬት የተፈጥሮ አቀማመጥ፣ በሰዎች ቋንቋ እና በዘር ተለይቶ ሊመደብ ይችላል። በእዚህ ምክንያትም ሰዎች የእኔ፣ ለእኔ እና እኔ ብቻ የማለት ፍላጎት ውስጥ ገብተው ሲባዝኑ ይታያል።
በምንም ይሁን በምን ዓለም ያበጀው ድንበር እንደታጠረ ተወስኖ የሚቀር ከሆነ ሰዎች ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ምሉዕ አድርገው ሊያገኙ አይችሉም። ምክንያቱም ሰው በምድር ሲኖር ጎደሎ ነገር አለው፤ ለሰው ልጅ ጎደሎ ሙላት የሚሆነው ደግሞ ራሱ ሰው ነው። አንዱ ሰው ያለውን ሌላው የለውም፤ ስለዚህ የአንዱን ጉድለት ሌላው እየሞላ በሰጥቶ መቀበል መርህ መኖር ለሰዎች የተሰጠ ተፈጥሯዊ ባህሪ እና አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ዓለም የፈጠረችውን ክፍፍል በሚገባና በትክክለኛ መንገድ ወደ አንድ ማምጣት ያስፈልጋል። አንድ መሆን የሌላውን ደስታ ለመደሰት፣ በሀዘኑ ለማዘንና ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ትልቅ አቅም ይፈጥራልና።
ዓለም ሰላም አጥታ በተጨነቀች ጊዜ ሁሉ መፍትሔው አንድነት እንደሆነ አውቃ ነበር። በፈረንጆቹ 1920 ላይ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ የአንድነት ተቋም የዛሬው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ተመሠረተ። ያኔ አንድ ሆኖ በአንድነት በችግሮች መፍትሄ ላይ መረባረብ ውጤት እንደሚያመጣ ተረጋገጠ፤ አንደኛው የዓለም ጦርነት ማክተሚያ በዚሁ ወቅት ሆኖ ተመዘገበ።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ብቸኛዋ የአህጉረ አፍሪካ ሀገር ኢትዮጵያ የመንግስታቱን ድርጅት ተቀላቀለች። ከመቀላቀል ባለፈ ብዝሀነትን በአንድነት የማስተዳደር ጥበቧ በድርጅቱ የአንድነት ተምሳሌት አደረጋት። ዛሬ እኛ እርስ በርስ ለመለያየት ምክንያት ልናደርግ የምንቃጣው ብዝሃ ብሔር፣ ቋንቋና እምነት በኢትዮጵያዊ የአንድነት ገመድ ታስሮ ስለነበር ዓለም በአድናቆት አይኑን ጥሎ ተሞክሮ እንዲወሰድበት በጉባኤው እንደመከረበት የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
በፈረንጆቹ 1945 ላይ ዓለም አቀፍ የአንድነት ተቋም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚለው ሲተካ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ከመሰረቱት ሀገራት አንዷ ሁና ስሟን በደማቅ ቀለም በዓለም መዝገብ ላይ አስፈራለች፤ የነጻነት እና የአንድነት ተምሳሌት ሀገር በመሆንም ትታወቃለች። በዚህም የመንግስታቱ ድርጅት ውስጥ በሰላም ማስከበር ሥራ በአፍሪካ የአንበሳውን ድርሻ መያዟ ይነገርላታል፤ በተጨባጭም ሰርታ አሳይታለች። በዳርፉር፣ በአብየ እና በደቡብ ሱዳን ላይ የነበራት ሚናም ለእዚህ የሰላም ማስከበር ሚናዋ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። በአንድነት ወዳድነቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ አንድነት የሰራች ኩሩ ሀገር መሆኗም ለዘለዓለም ይዘከራል።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለአፍሪካ አንድነትና ሰላም የምትሞግት ብቸኛ ተወካይ ነበረች ቢባልም ማጋነን አይሆንም። በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ ሀገራት በመዲናዋ አዲስ አበባ እንዲከትሙ የፍቅር ጥሪዋን በክብር ለአፍሪካ ሀገራት አቀረበች። ሀገራቱም የነጻነት እናታቸውን ጥሪ ተቀብለው ከልዩነት መንደር ተሰብስበው በአንድ ጎጆ ተጠለሉ። በአንድ ጉዳይ ያውም አንድነት መፍጠር ላይ በጋራ መከሩ። ምክራቸው ሰምሮ የአፍሪካ ኅብረትን የአፍሪካውያን የአንድነት ምሰሶ አድርገው አቆሙ። ይህም በኢትዮጵያ የአንድነት ሰባኪነትና ተምሳሌትነት እውን ሆነ።
የአንድነት እሳቤ ብዙ የተራራቁ ልቦችን፣ የማይጣጣሙ ሀሳቦችና የተበታተኑ ጉዳዮችን በማቀራረብ አንድ ላይ እንዲሆኑ ያደርጋል። ኢትዮጵያ በየፊናቸው ተበትነው በቅኝ ግዛትና በሰላም እጦት እንዲሁም በሎች ችግሮች ውስጥ የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን በአንድ ሀሳብ እንዲስማሙ አድርጋለች። በእዚህም አፍሪካውያን አንድ እንሁን፤ አንድ ሆነን ሰላማችንን እናስጠብቅ፤ አንድ ሆነን ጫናን እንመክት፣ ቅኝ ግዛትንም እናሽቀንጥር ብለው ተስማሙ። በጋራ በመስራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግም ችግሮችንና የችግሮችን መፍትሄ ማምጫ መንገድ የጋራ አደረጉ።
በአፍሪካ ኅብረት መመስረትና የጋራ አቋም ይዞ ለመስራት መሰብሰብ በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ነው የሚባል የሚዘከር ትልቅ ለውጥና ዕድገት ባይመጣም ሀገራቱ ከቅኝ ግዛት ተላቀዋል። አፍሪካ ለወደፊት እንደ አህጉር ለውጥና ዕድገት ማምጣት የሚትችልባቸው ተስፋዎች ተፈጥረዋል። ሀገራቱ ሰላም ማስፈንና ርሀብን ሙሉ በሙሉ ታግለው ማሸነፍ ቢሳናቸውም እንኳ የአንዱን ሕመም አንዱ የሚረዳበት የጋራ አውድ ተፈጥሯል። ለችግሮቻቸው መፍትሔ የሚሏቸውን ሀሳቦች የሚያንሸራሽሩበት የራሳቸው መድረክም አሏቸው።
የራሳቸውን ፖለቲካዊ ችግር በራሳቸው መፍታት የሚችሉበት መድረክም ተፈጥሯል። ይህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን የሰላም እጦት ለመፍታት በተደረሰው የሰላም ስምምነት በተግባር ተረጋግጧል። ጅምሩ ወደ ፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካ ትርጉም ያለው ቦታ እንዲሰጣት ጥያቄዎችን አቅርባ የከፍታ ጥያቄ የምታቀርብበት የአንድነት ድምጽ ተፈጥሯል። ለዚህም ቢሆን ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ የጎላ ነው። እሷ በርትታ ሌሎችን ታበረታለች፤ ሰርታ ታሰራለች። በአፍሪካ ምድር ሁልጊዜም የአንድነትና የሰላም መሪ ተዋናይ ሆና ታበራለች።
ኢትዮጵያ ከአህጉር እስከ ዓለም አቀፍ ደርሳ የአንድነት ሰባኪና መሪ ያደረጋት ያኔ የነበራት የውስጥ አንድነቷ ነው። የአንድነት ትርጉም በጥልቅ የገባቸው ኢትዮጵያውያን "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" እያሉ የትንሿ ሸረሪት ድር በሃያልነቱ የሚፈራውን ጉልበታም አንበሳ አስሮ እንደሚይዝና እንደሚያንበረክክ በመግለጽ የአንድነትን ትርጉም አርቅቀውና ከፍ ባለ ቦታ አስቀምጠው እናገኛለን። ይህንን ከአባባል ባለፈ በትርጉም ኑረውበት አሳይተውናል። ለእዚህ የአድዋ ድል ህያው ምስክር ነው። እስከ አፍንጫው የታጠቀን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያዊያን ምንም ዘመናዊ መሳሪያ ሳይዙ በአንድነት ሆ ብለው በመውጣት አሸንፈው ድል ተቀዳጅተዋል። አንድነት ሀይል መሆኑን ከዚህ በላይ ማሳያ ማቅረብ አያስፈልግም።
ለዚህ ነው የኢትዮጵያ የአንድነት ተምሳሌት ጎልቶ በዓለም ፊት አንጸባራቂ ሆኖ የታየው። ይህ በዘመን ጅረት ሲተረክ እየለመለመ የሚሄድ እንጂ የእሳት ልጅ አመድ ሆኖ እንዲቀር ዛሬ ያለነው ትውልድ መፍቀድ የለብንም። የትላንት የውስጥ ኅብረትና እንድነታችን ዛሬ እርስ በርስ በመከፋፈል ሊቀየር አይገባም።
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከጉባኤ ባሻገር ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም እንዳለው ለማስታወስና ለማሳየት ያህል ይህን ጽሑፍ አዘጋጀሁ። ጽሁፉ ትላንት ኅብረቱ ሲመሰረት የነበረንን የአንድነት መንፈስ በጥቂቱም ቢሆን እንድናስታውስ ያደርጋል። ከትላንት መዝገብ መልካሙንና በዓለም ፊት ቀና የሚያደርገንን ጉዳይ እንጂ አንገታት የሚያስደፋ ታሪክ አንመዝም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ለወትሮም የምንታወቀው አንድ ሆነን ሌሎችን አንድ በማድረግ፤ ሰላማዊ ሆነን ሰላምን በማስከበር ነው።ትላንት የተበተነ ዛሬ ሲሰበሰብ እንጂ ትላንት አንድ ሆኖ ዛሬ መበተንና መፈረካከስ የሚያስከትለው ውድቀት በቀላሉ መታከም እንደማይችልም ለአፍታ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደቤታችን መጥተው በአንድ ጎጆ ስር ተቀምጠው የመነጋገራቸው አንዱ ምክንያት ትላንትም ዛሬም ሌላ ነገር ሳይሆን አንድነታችንና ሰላም ወዳድነታችን ነው። ይህንን አጥብቀን ልንይዝ፤ ከጎበጠም ፈጥነን ልናቃናው ይገባል። ሰላም!