86ኛው የሰማእታት ቀን በየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
86ኛው የሰማእታት ቀን በየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ ያወረሱትን አኩሪ ታሪክ በአንድነትና በአብሮነት በመቆም ሊደግመው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቢቤ ገለጹ፡፡
86ኛው የሰማእታት ቀን በየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
ቀኑን በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰማእታት ሀውልት በመገኘት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት አባቶቻችን ከ86 ዓመታት በፊት ፋሺስት የጣሊያን ሰራዊት ቂም ይዞ ከሰላሳ ሺህ በላይ ዜጎቻችንን በአዲስ አበባ መጨፍጨፉን የሚታወስበት ይህን ቀን ስናከብር የአባቶቻችንን አኩሪ ገድልን በመዘከር ነው ብለዋል፡፡
አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ሀገራችን በአፍሪካ በነጻነት ፀንታ እንድትቆይ ማድረጉን ያወሱት ከንቲባ አዳነች ይህን አኩሪ ታሪክ መተረክና ማስታወስ ብቻ ሳይሆን ወጣቱ ትውልድ ለሀገሩ እድገት በአንድነትና በጋራ በመቆም የራሱን አሻራ ሊያኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በዛሬው ቀን የደረሰብን የከፋ አደጋ ኢትዮጵያውያንን አላንበረከከንም ያሉት ከንቲባዋ ኢትዮጵያ የነፃነት ሀገር ሆና እንድትቀጥልና እንድንኮራበት አድርጎናል፡፡
ይህን በደም የተገነባ ነፃነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀገራችን ከጉስቁልና ተላቃ የምትፈልገው የእድገት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ወጣቱ ትውልድ የራሱን አሻራ በማኖር ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በመነጋጋር በመግባባት መፍታትና በጋራ የራሳችንን ታሪክ ለመስራት መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዘዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው የሰማእታቱን ቀን የምናስበው ለወጣቱ ትውልድ የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ ለማውረስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህን እልቂት ተገቢ እንዳልሆነ የተገነዘቡ የጣሊያን ወንድሞቻችን በአሁኑ ወቅት በሮም ከተማ በማውገዝ እንደሚዘክሩት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ገልጸዋል፡፡
በመታሰቢያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አባላትና በርካታ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡