ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 11/2015 በኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጀት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት የደረሱበት የሰላም ስምምነት በቅርቡ ከተከናወኑ አዎንታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጫቸው አመልክተዋል።

የሰላም ስምምነቱን ገቢራዊ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው የተግባር እንቅስቃሴም የሚበረታታና ሊደገፍ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሰላም ስምምነቱ ያለውን ድጋፍ በማስመልከት ዛሬ ማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍና የልማት ትብብር ድጋፎች በስፋት ለማቅረብ ድርጅታቸው ቁርጠኛ ስለመሆኑም ዋና ጸሐፊው አረጋግጠዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶች በኢትዮጵያ በጦርነቱ ሳቢያ የደረሰውን ችግር በቅጡ ተገንዝበው ለመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በተለይም በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ነው ያሉት።

በአፍሪካ አሁንም በርካታ የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም በአህጉሩ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።

ለአብነትም የሊቢያ የተኩስ አቁም፣ የደቡብ ሱዳን እና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሰላም ስምምነት እንዲሁም በሶማሊያ እየታየ ያለው የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ መልካም ጅማሮ መሆኑን ተገንዝበናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም