የአየር ንብረት ፋይናንስ-አፍሪካውያን ገፍተው ያልሄዱበት መንገድ

2075

/በገዛኸኝ ደገፉ/

የአፍሪካ ቀንድ ከ40 ዓመታት ወዲህ ተከስቶ አያቅም የተባለለትን የድርቅ አደጋ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል።

የድርቁ አደጋ የከፋበት የአፍሪካ ቀንድ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ተሸክመዋል።

በተጨማሪም የከተሞች መስፋፋትና የከተሜነት የኑሮ ዘይቤን እያስተናገደች ባለችው አፍሪካ የኃይል እጥረት፣ በቂ የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ አለመኖር፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት፣ ሥራ አጥነት ብሎም የወንጀሎች መስፋፋት አሕጉሪቱን ክፉኛ እየፈተኗት ይገኛሉ።

የገጠር መሬት ምርታማነት መቀነስ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚደረገው ፍልሰት አንደኛው ገፊ ምክንያት ሲሆን ለመሬቱ ምርታማነት መቀነስ ሰበብ ተደርጎ በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥና የበረሃማነት መስፋፋት የሚወልዳቸው የውኃ ኃብት መቀነስና ለተከታታይ ዓመታት የሚዘልቁት የድርቅ አደጋዎች መሆናቸው ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

እንደ አህጉር ከ4 በመቶ ያነሰ የካርቦን ልቀት ያላት አፍሪካ 65 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ የችግሩ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ መሆን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚህ ችግር ሙሉ ለሙሉ መውጣት ባይቻልም ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነስ እንዲቻል አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ኃብትና ወጣት የሰው ኃይል በማስተሳሰር ለውጥ ማምጣት ግድ ይላታል። በአፍሪካ የማይቀረውን የከተሞች መስፋፋትም ሆነ የህዝቦቿን የመልማትና የመለውጥ ፍላጎት ማሟላት ካለባት የአየር ንብረት ፋይናንስን የበለፀጉ ሀገራት ገቢራዊ ሊያደርጉት ይገባል።

የአየር ንብረት ፋይናንስ (Climate Finance) የአካባቢ፣ ብሔራዊ ወይም ድንበር ተሻጋሪ ፋይናንስን የሚመለከት ሲሆን ከሕዝብ፣ ከግል እና ከአማራጭ የገንዘብ ምንጮች የተውጣጣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ እና ለማስተካከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው።

የኪዮቶ ፕሮቶኮል እና የፓሪስ ስምምነት ደግሞ ሰፊ የገንዘብ አቅም ካላቸው አገራት አነስተኛ የኃብት አቅም ላላቸው እና ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ የሚጠይቅ ስምምነት ነው። ስምምነቱ “የጋራ ግን ደግሞ ልዩነት ያለው ኃላፊነትና አቅም” በሚለው መርህ መሰረት ያደጉ አገሮች አዳጊ አገራትን ለመርዳት የገንዘብ ምንጮችን እንዲያቀርቡ ይጠይቃል።

ፋይናንሱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ወሳኝ ድጋፍ እንደሚሆን ታምኖበታል። ምክንያቱም ልቀትን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ላቅ ያለ የኢንቨስትመንት አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ። በተመሳሳይ ከአሉታዊ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎች ጋር ለመላመድ እና ተለዋዋጭ ጫናዎችን ለመቀነስ የአየር ንብረት ፋይናንስ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።

ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተዘጋጅቶ የቀረበው የምእተ ዓመቱ የልማት ግብ ሰነድም ሆነ በቅርቡ በሚጠናቀቀው ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ለጉዳዩ ከፍ ያለ ትኩረት ቢሰጠውም እስካሁን ግን የፈየደው ነገር የለም።

አፍሪካ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመላመድ ዓመታዊ 41 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የፋይናንስ ክፍተት ይገጥማታል። ይህን ክፍተት ለመሙላት አዲስ አበባ እያስተናገደች ባለችው 36ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የአየር ንብረት ፋይናንስ ገቢራዊ ማድረግን ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን እንዳለበት የአንድ ዘመቻ (ONE Campaign) አጽንኦት ሰጥቶ ምክረ ሃሳቡን ሰንዝሯል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የአንድ ዘመቻ ዳይሬክተር ዶሪን ኒኒናሃዝዌ የአፍሪካ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመላመድ ፋይናንስ ድጋፍን በማረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ ተጽዕኖ የመቋቋም አቅም እንዲገነቡ መክረዋል።

አፍሪካ ባልፈጠረችው የአየር ንብረት ለውጥ ህዝቦቿ ለከፋ ጥቃት እየተዳረጉ ይገኛሉ። ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች የበለጸጉ አገሮች የገቡትን የማላመድ ፋይናንስ ድጋፍ ቃል እንዲፈጽሙ ከማግባባት ባለፈ ማሳሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ይህ ማለት እኤአ ከ2020 እስከ 2025 በዓመት 100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመተውን ግብ የማሳካት ተግባር የሚጠይቅ ነው። ከዚህ ባሻገር በቀጣዮቹ ዓመታት በተጨመሩ መዋጮዎች የሚስተዋሉ ጉድለቶችን መፍታት እና በግብጿ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ ባስተናገደችው COP-27 ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለመላመድ በእጥፍ ፋይናንስን የማቅረብ ቁርጠኝነት የማቅረቢያ ዕቅድ ሊነድፉ ይገባል ነው ያሉት።

የአፍሪካ አገሮች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ጋር ሲታገሉ ቢቆዩም አሁን ላይ “አፍሪካ በአፈፃጸሙ ላይ መጠነኛ መሻሻል አሳይታለች” ብለዋል።

እናም በ36ኛው የመሪዎቹ ጉባዔ የተገኙ ስኬቶች እና የጠፉ ዕድሎች እንዲሁም የድርጅቱን ዓላማዎች ለማሳካት በአየር ንብረት ፋይናንስ በጥልቀት መክረው ለተሻለ ስኬት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ በአየር ንብረት ምክንያት የሚፈጠሩ መፈናቀልን ለመግታት የተሻሻሉ የመላመድ እና የተጽዕኖ ቅነሳ ተነሳሽነት ገቢራዊ ለማድረግ በአገራት መካከል ጠንካራ አጋርነትን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል።

በተለይ በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በተፈጥሮ ሃብት ላይ ኑሯቸውን መሰረት ባደረጉ ህዝቦች ላይ አውደ-ተኮር መላመድ እና የመቋቋም አቅም ግንባታ መፍጠር ይገባል። ለዚህ ደግሞ መላመድን የሚደግፉ ፋይናንስ ለማግኘት የሚረዱ መመሪያዎች ይበልጥ የተፍታቱ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ ቪቶሪኖ ይሞግታሉ።

ከ 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ በተካሄደው ከፍተኛ የውይይት መድረክ (High-Level Forum) ላይ ዳይሬክተሩ እንዳሉት በሻርም ኤል ሼክ በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ መላመድን፣ መከላከልን እና ዝግጁነትን ለማሻሻል ዓለም አቀፍ ትብብር ማጎልበት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አውስተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ያወጣቸው የስምምነት ማዕቀፎች (United Nations Framework Convention on Climate Change (UNFCCC)) በርካታ ዝርዝርና ሚዛናዊ አካሄዶችን የያዙ ናቸው። ያም ሆኖ አተገባበራቸው እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ የሚታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል። በዚህም ቦረና ዞንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

የአየር ንብረት መዛባት፣ የሙቀትና የባህር ጠለል መጨመር፣ ጎርፍ፣ ድርቅ እንዲሁም ያልተገመቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመቀነስ የአየር ንብረት ፋይናንስ ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማሙበታል።

ዳሩ ግን አገራትን፣ አህጉርን፣ ዓለምን እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግዙፍ ኩባንያዎችን ያስተሳስራል የተባለለት የአየር ንብረት ፋይናንስ በቅጡ ገቢራዊ ማድረግ ባለመቻሉ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ በርካታ ህዝቦች ዳፋውን ለመጋፈጥ ተገደዋል።

የአየር ንብረት ፋይናንስን በመተግበር በመስኩ የተጎጂዎችን ቁጥር ሊቀንሱና የዓለምን ሥነ-ምህዳር ከተቻለ ወደ ቀድሞው ሊመልሱ አሊያም አሁን ባለበት አረጋግተው ሊያቆዩ የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል።

ለአብነትም ለድሃ ሃገራት አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች ተገቢውን ዋጋ በመክፈል የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን እንዲቋቋሙ ማድረግ ከአማራጮቹ መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ግዙፎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለሚያስወግዷቸው በካይ ጋዞች ተመጣጣኝ የጤና ሥርዓት በመዘርጋት የታዳጊ ሃገራት ዜጎችን የጤና አገልግሎት ማሻሻል ሌላው አማራጭ ነው። የተፈጥሮ ኃብቶችን የሚጎዱ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተፈጥሮን በሚንከባከቡ ዘዴዎች መተካት እንዲሁም ብክለትን የሚያስቀሩ የምርት ሂደቶች መለማመድ ጥቂቶቹ የመፍትሄ አማራጮች ተደረገው የሚወሰዱ ናቸው።

በፓሪስ ከተደረሰውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ቀደም ብሎ በፈረንጆቹ 1994 ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (Global Environment Facility-GEF) COP-16 ዓለም አቀፍ ጉባዔ በኋላ በ2010 አረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ (Green Climate Fund-GCF) እንዲሁም በ2001 ደግሞ ልዩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ (Special Climate Change Fund-SCCF) እና የመላመድ ፈንድ (Adaptation Fund-AF) የተባሉ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ቢሆንም ስለጉዳዩ የሚያስረዱ ተከታታይ ስብሰባዎች ከማዘጋጀት በዘለለ ብዙ ርቀት መጓዝ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በቅርቡ በአለም ባንክ አሰባሳቢነት በኬንያ ናይሮቢ ተዘጋጅቶ በነበረው የአህጉሪቱን መሪዎች ባለሃብቶችንና ምሁራንን ባካተተውና “One Planet Summit” በተሰኘ መሰል ጉባዔ ላይም አፍሪካውያን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚገጥማቸውን ችግሮች ተከላክለው ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን እንዲያፋጥኑ ካስፈለገ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ አዘጋጅተው መተግበር እንደሚኖርባቸው መግባባት ላይ የተደረሰ ቢሆንም አሁንም ጥያቄ ያስነሳው አፈጻጸሙ ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል።

ክላይሜት ፖሊሲ ኢኒሽየቲቭ የተባለ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመለክተው አፍሪካ እንደ ፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር ከ 2020 እስከ 2030 ባሉት አሥር ዓመታት 2 ነጥብ 8 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር አሊያም በየዓመቱ ከ2 መቶ ሃምሳ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያስፈልጋት ሲሆን አህጉሪቱ ከዘርፉ እያገኘችው ያለው ገንዘብም ከሚያስፈልጋት 12 በመቶውን ወይም 30 ቢሊየን ዶላር ብቻ ስለመሆኑ አስነብቧል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁመው ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ተግባራት እንዳሏት የሚያትተው ሪፖርቱ ከአየር ንብረት ፋይናንስ የሚገኘው ገንዘብ በትራንስፖርት፣ በኃይል ልማት፣ በኢንዱስትሪ ብሎም በግብርና፣ በአፈርና በደን ኃብት አጠቃቀም ውጤታማ በሆነ መንገድ ከዋለ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ኃብቶች መንከባከብ ከማስቻሉም ባለፈ ላቅ ያለ ፋይዳ ይኖራዋል ብሏል። ይህ ሲሆን የሥራ ዕድል በመፍጠር የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስ ለአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖው ያስረዳል።

ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ገቢራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራን የማስፋፋትና የተጎዱ አካባቢዎችን የማከም ሥራ እንዲሁም አይቀሬ የሆኑትን ከተሜነትና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ታሳቢ ያደረጉ የአየር ንብረት ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ለአፍሪካ ሃገራት እየፈጠረው ያለው በጎ ተጽዕኖ በግልጽ እየታየ ነው።

ይህ የኢትዮጵያ ጥረት ግን በአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲደገፍ አገራዊና የተቀናጀ አሕጉራዊ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ከአጠቃላይ የአፍሪካ አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ግብጽ ብቻ 151 ቢሊየን ዶላር ከአየር ንብረት ንብረት ፋይናንስ ማግኘት እንደሚኖርባቸው የክላይሜት ፖሊሲ ኢኒሽየቲቭ ሪፖርቱ ይገልጻል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በመጭው የCOP-28 ጉባዔ የራሷንና የአፍሪካን ፍላጎት የሚያስጠብቁ የፋይናንስ ትልሞችን የመንደፍ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡

የ COP-27 ጉባዔ ለአፍሪካ ያስገኘውን ውጤት እና አንድምታ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አስተባባሪ በሆኑት በኬንያው ፕሬዝዳንት ሰብሳቢነት በኅብረቱ የአዲስ አበባ ጉባዔ ላይ በጥልቀት ይገመግማል ተብሎ ይጠበቃል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ጥረቷን የሚያጎለብት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ጠንካራ ተሳትፎ ልታደርግ ይገባል።

የአፍሪካ አገራት ገፍተው ረጅም ርቀት ያልሄዱበት የአየር ንብረት ፋይናንስ እና ሌሎች የድጋፍ አማራጮችን በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት በመጠቀም የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቋቋሙበት ጠንካራ አቅም ሊገነቡ ግድ ይላቸዋል።

በእርግጥም አፍሪካውያን መሪዎች በሚያደርጉዋቸው ስብሰባዎች በየማዕዝናቱ በድርቅ ሳቢያ ለምግብ እጦት የተዳረጉ ህዝቦቻቸውን የሚታደጉበት ሁነኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ዘዴ ነድፈው ረጅም ርቀት ሊጓዙ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም