ዛሬ የሚጀመረው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል

4181

"የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መቀላጠፍ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ወደ ሥራ የገባውንና 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ሕዝብ በንግድ ለማስተሳሰር የታለመውን የንግድ ቀጣና ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይመክራል።

በተለይም ደግሞ የጋራ የጉምሩክ ሥርዓትና ወጥ የታሪፍ አስተዳደር በአህጉሪቷ ለመተግበር ትኩረት ይደረግበታል ተብሏል።


ሌሎችም የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነትን የሚያቀጭጩ አሰራሮች ነቅሶ በማውጣት የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር ምክክር አድርገው አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል።


የአፍሪካ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ


በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተው ድርቅና ረሃብ እንዲሁም በዩክሬንና በሩስያ ጦርነት ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀው የአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግር እልባት በሚሰጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሏል።


በተለይም ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ሥራ ለማሳለጥና በአህጉሪቱ ዘመናዊ የእርሻ ሥራ በሚስፋፋባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።


ይህም በዘላቂነት የአህጉሪቱን የምግብ ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል ተብሏል።

በመሆኑም የዛሬው ጉባዔ ትኩረቱ በዚሁ የምግብ ዋስትና ሁኔታ ላይ እንደሚሆን ብዙ ግምት ተሰጥቶታል።


የአፍሪካ የ2063 አጀንዳ አፈጻጸም

ባለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት የተጣለውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ ከግምት በማስገባት የተሰሩ ሥራዎች ይገመግማል ተብሏል።

ለቀጣይ አሥር ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚችሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጎ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ነው የተገለጸው።


በተለይም ደግሞ ዋና ዋና የሚባሉ ስኬቶችን በመገምገምና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት መጪውን አሥር ዓመት የተሻለ ለመፈጸም የሚያስችል የትግበራ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል።


ከዚህም ባሻገር አፍሪካ በፋይናንስ ራሷን እንድትችል እየተደረገ ያለውን ጥረትም ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአብነትም የኅብረቱ ሰላም ፈንድ የሚደረገው የአባል አገራት መዋጮና አገራት ከታክስ ገቢያቸው ለኅብረቱ በማዋጣት አጠቃላይ የኅብረቱን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውም ጉዳይ ምክክር ሊደረግበት የሚችል ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በቻድ፣ በካሜሮን፣ ኒጀር፣ በናይጄሪያ አካባቢው ከጽንፈኝነት ጋር በተያያዘ በርካታ የጸጥታ ችግሮች እየተከሰቱ ሲሆን ይህም ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍልም የትጥቅ ትግል መቀስቀሱ የተዘገበ ሲሆን ይህም አገሪቱን ከሚያዋስኑ አገራት ጋርም አለመረጋጋት ፈጥሯል። በሰሜን ሞዛምቢክ ያለው የጸጥታ ችግርም አሁንም እልባት ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ትግበራ ሂደት ላይ ናቸው፤ ሱዳን ሕዝባዊ አስተዳደር ለመመሥረት የሽግግር ትግበራ ላይ ናት።

በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት በእነዚህና በሌሎች የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም