ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገሪቱን ቱሪዝም ለማሳደግ የበኩሌን ጥረት እያደረግኩ ነው አለ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ የበኩሌን ጥረት እያደረግኩ ነው አለ። ኢትዮጵያ በዓለም የተመዘገቡትን 12 ቅርሶች ጨምሮ በርካታ የባህል፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ ባለቤት ብትሆንም የአገሪቱ  ጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይናገራል። አየር መንገዱም እነዚህን መስህቦች ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል ሰፊ አቅም ያለው ተቋም ቢሆንም አስካሁን ግን በዚህ ረገድ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሰራ ነው የገለፀው። የአየር መንገዱ የአሜሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ወርቁ ከኦል አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአሁኑ ወቅት ግን አየር መንገዱ የአገሪቱን ቱሪዝም ለማጠናከር የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን እንደመተላለፊያ የሚጠቀሙ የተለያዩ አገራት መንገደኞችን በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ቢያንስ አንድ ቀንና ከዚያ በላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር ጥረት ተጀምሯል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ወደሀገሪቱ የሚመጣው ቱሪስት እንዲጨምር ያደርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም ለአየር መንገዱም መልካም አጋጣሚ በመሆኑ እድሉን ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል። አቶ ንጉሱ ኢትዮጵያን መጎብኘት የሚፈልጉ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ካሉ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ በዜና አውታሩ በኩል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም