ቀጥታ፡

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ እድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ እድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ ።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) ለአፍሪካ የምግብ ዋስትናና የምጣኔ-ሀብት እድል በር ለከፈቱ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሰጠው "የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" አዲስ ሊቀ-መንበር ሾሟል።

የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ሚሪሾ ኪኪወቴ "የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሶግ ኦባሳንጆ ለአዲሱ "የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ሚሪሾ ሃላፊነቱን አስረክበዋል።

በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ሽግግር ቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትናን እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለነገ የማይባል ስራ መሆኑን በመግለጽ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች አገራት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ እድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሶግ ኦባሳንጆ በበኩላቸው፤ሽልማቱ የአፍሪካን ግብርና ለማዘመንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

ሽልማቱ በአህጉሪቱ በግብርና እና ምግብ ዋስትና አስተዋጾኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው በእውቀት፣በቴክኖሎጂና ልምድ ልውውጥ ለአህጉሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው እንስተዋል።

አዲሱ "የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ሚሪሾ፤በተሰጣቸው ሃላፊነት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የአፍሪካን ግብርና እና የምግብ ዋስትና ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካ የምግብ ሽልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ የምግብ ሽልማት ውስጥ ካሉት ኮሚቴዎች መካከል የቀድሞ የኢሴክስ መስራች ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን ይገኙበታል።

"የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" የአፍሪካን ግብርና ለሚያሸጋግሩ ግለሰቦችና ተቋማት 100 ሺህ ዶላር የሚሸልም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም