የጊኒቢሳው ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የኢትዮጵያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የጊኒቢሳው ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የኢትዮጵያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጎበኙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 10/2015 የጊኒቢሳው ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የኢትዮጵያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጎበኙ።
የጊኒቢሳው ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የኢትዮጵያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ያደረጉት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ነው።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ተቋም እውን በማድረግ ላይ መሆኗን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ለፕሬዚዳንት ሲሶኮ ገልፀውላቸዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አመራሮችም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቅ የአሸባሪዎችን ሴራ አስቀድሞ የሚያከሽፍ የሰው ኃይልና የዲጂታል አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።
በተለይም በወሳኝ ተቋማት ላይ የሚሞከሩ መጠነሰፊ የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብቁ የሰው ኃይልና በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ተቋማትን መገንባቷም ለፕሬዚዳንቱ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል የጊኒቢሳው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የተሳካ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው ውይይትም በ1960ዎቹ የተጀመረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው ያብራሩት።
ፕሬዚዳንቱ በተለይ ጊኒቢሳው ከኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግ መግለፃቸውን ተከትሎ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን እንዲጎበኙና ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ከሰው ኃይል እስከ ቴክኖሎጂ የደረሱበት ደረጃ አስደማሚ መሆኑንና ጊኒቢሳውም ይህንን ተሞክሮ እንደምትወስድ መግለፃቸውን ነው የጠቀሱት።
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ቀድሞውንም የሚያደንቋት ቢሆንም በአሁኑ ጉብኝታቸው ታላቅ ሀገር መሆኗን በተጨባጭ መመልከታቸውን እንደገለፁም አምባሳደር ፍስሐ ተናግረዋል።
ሌላኛው ፕሬዚዳንቱ የጎበኙት ተቋም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሲሆን፥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የላቁ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ እና ከሀገር አልፎ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር የሚችል የፖሊስ ኃይል መፈጠሩን ገልጸውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ኢትዮጵያ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት አስደናቂ ለውጥ በማድረግ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካ የምትተርፍበት ደረጃ ላይ መድረሷን መመልከታቸውን መናገራቸውን አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ተናግረዋል፡፡
ጊኒቢሳው በአሳ ሀብት ልማት የምትታወቅ ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ልምዷን የምትወስድበት ሁኔታ እንዲፈጠር መግባባት ላይ መደረሱኑም ነው አምባሳደር ፍስሐ የገለፁት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለቱን ሀገራት የአየር ትራንስፖርት ትስስር የሚፈጥርበትና የሚያጠናክርበትን የትብብር ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ መግባባት ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ መምሪያን የጎበኙ ሲሆን፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከብርና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱን ለፕሬዚዳንቱ አብራርተውላቸውል።
ፕሬዝዳንቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያካሄደው ሪፎርምና አሁን ያለበት ቁመና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ እንደሚሆን መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል።