የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ መሆኑን የሀገር አቀፍ የትምህርት ፈተናና ምዘናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዝአብሔር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ከዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ይፋ ሆኗል። ምደባው የተማሪዎችን ውጤት፣ የትምህርት ዓይነት፣ የዩንቨርስቲ ምርጫ፣ የዩንቨርስቲዎችን የቅበላ አቅም፣ የወንዶችና የሴቶችን ምጠና ማዕከል ባደረገ እንዲሁም የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ያገናዘበ መሆኑን ነው ያመላከቱት። ዓይነ ስውራንን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ አካል ጉዳተኞችን/ በተጨማሪም የጤና እክል ያለባቸው እና ከታወቀ የመንግስት ሆስፒታል የሜዲካል ቦርድ ማረጋገጫ ያቀረቡት ላይ የማጣራት ስራዎችን ካካሄደ በኋላ ምደባው እንደተዘጋጀም እንዲሁ። በዚሁ መሰረት በዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የማለፊያ ነጥቡን  ያለፉ 138 ሺ 283 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ 75ሺ 338 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 213 ሺ 621 ናቸው። ከነዚህም መካከል 98 ሺ 576 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችና 51 ሺ 229 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 149 ሺ 805 ተማሪዎች ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ባሉት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በአጠቃላይ የሚመደቡ ይሆናል። ከነዚህም በኤጀንሲው በኩል በ43ቱ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 95 ሺ 681 የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም  51ሺ 066 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 146 ሺ 747 ተማሪዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል። ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት የትምህርት ተቋማት በሚሄዱበት ወቅትም የነገዋ ኢትዮጵያ በትከሻቸው ላይ መሆኗን በመገንዘብ ለትምህርታችሁ ትኩረት እንዲሰጡም አቶ አርአያ አሳስበዋል። ተማሪዎች ምደባችሁን በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉም ነው የገለፁት።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም