በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ላይ የሚሰራ 'የብሉ ዲል ፕሮጀክት ' ሁለተኛው ምዕራፍ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ላይ የሚሰራ 'የብሉ ዲል ፕሮጀክት ' ሁለተኛው ምዕራፍ ይፋ ሆነ
የካቲት 10 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ላይ የሚሰራ አለማቀፍ 'የብሉ ዲል ፕሮጀክት' ሁለተኛ ምዕራፍ ይፋ ሆነ ፡፡
"ብሉ ዲል ፕሮጀክት" በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሃ አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመን በኔዘርላንድ መንግስት አማካኝነት የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፕሮጀክቱ ጋር በተለይ በውሃ ምደባ ፣ በተፋሰስ እቅድ ትግበራ ፣ በውሃ ጥራት በተፋሰስ መረጃ አስተዳደር ዙሪያ በጋራ በመስራት ላይ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛና በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር በተገኙበት "የብሉ ዴል ፕሮጀክት" ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ እንዳሉት ሁለተኛው ምዕራፍ የብሌ ዴል ፕሮጀክት ከ2023 እስከ 2026 ለቀጣዮቹ ለሶስት ዓመት የሚቆይ ነው፡፡
"የብሉ ዲል ፕሮጀክት" የውሃ አስተዳደር የመረጃ ሥርዓትን በአቅም ግንባታ መርሃ ለማሻሻል ያለመ የኔዘርላንድ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዉሃ ሀብት እንክብካቤና ጥበቃ ካልተደረገለት እየጠፋ እንደሚሄድ የገለጹት ዶክተር አብርሃ፤ በአዋሽ፣ በዓባይና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በትብብር ፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ፤ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት መመሪያና መመዘኛ በማዘጋጀት ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥር እናደርጋለን ብለዋል፡፡
"ብሉ ዲል ፕሮጀክት" የረጅም ጊዜ አጋር መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብርሃ፤ ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ክልሎችን፣ የዉኃ ተጠቃሚዎችንና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የተፋሰስ ዕቅድ ይዘጋጃል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር በበኩላቸው ኢትዮጵያን በውሃ አስተዳደር በኔዘርላንድ ብሉ ዲል ፕሮጀክት በኩል ተጠቃሚ እናደርጋታለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ የውሃ ተፋሰሶች በሦስቱ ተፋሰሶች ትኩረት አድርጎ በውሃ አያያዝ ዙሪያ ለባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡