36ኛውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ 852 ጋዜጠኞች እየዘገቡት ነው - ኢዜአ አማርኛ
36ኛውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ 852 ጋዜጠኞች እየዘገቡት ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10 ቀን 2015 በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘውን 36ኛውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ 852 ጋዜጠኞች እየዘገቡት መሆናቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደሴ ከፋለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዘንድሮውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ 852 የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እየዘገቡት ነው።
ከእነዚህም መካከል 450ዎቹ ተቀማጭነታቸውን በተለያዩ አገራት ያደረጉና ለዘገባው የመጡ የተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ሲሆኑ 70ዎቹ ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ወኪሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የቀሩት 332 ጋዜጠኞች ደግሞ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም አምና በዘገባው ከተሳተፉት 700 ጋዜጠኞች ጋር ሲነጻጸር ከ21 ነጥብ 1 በመቶ በላይ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመዘገብ የመጡ የውጭ ጋዜጠኞች ቁጥር 332 እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮው 450 ጋዜጠኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ36 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ጋዜጠኞች ቪዛ እንዲያገኙና የሙያ መሳሪያዎቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።