የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ኃይል አማራጭነት የሚቀይር ማሽን ለባሌ ዞን ወጣቶች ተበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ኃይል አማራጭነት የሚቀይር ማሽን ለባሌ ዞን ወጣቶች ተበረከተ
ጎባ የካቲት 10/2015 (ኢዜአ) የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ከሰል እና እንጨት መሳይ ማገዶ በመቀየር ለኃይል ምንጭነት መቀየር የሚያስችል ማሽን ለባሌ ዞን ወጣቶች ማበርከቱን የኦሮሚያ ቡና አምራቾች 'ዩኒየን' ገለጸ።
'ዩኑየኑ' የቡና ተረፈ ምርቶችን ወደ ከሰልና እንጨት የሚቀይርና ግምታዊ ዋጋቸው 7 ሚሊዮን ብር የሆኑ ሶስት ማሽኖችን በመግዛት በማህበር ለተደራጁ የባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ወጣቶች ድጋፍ አድርጓል።
ማሽኑ ተረፈ ምርቱን ወደ ኃይል አማራጭነት ከመቀየር በተጓዳኝ የቡና አምራች ገበሬዎች ተረፈ ምርቱን ለማስወገድ ያወጡ የነበረውን ወጭ እንደሚያስቀር ተገልጿል።
የኦሮሚያ ቡና አምራቾች 'ዩኒየን' ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳዲ እንዳሉት ዩኒየኑ የቡና አምራቾች የሚያመርቱትን ምርት ለገበያ በማቅረብ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ አትኩሮ እየሰራ ነው።
አምራቹ የቡና ምርታመነትን በመጨመር ገቢውን እንዲያሻሽል ከማድረግ በተጨማሪ ይጣል የነበረው ተረፈ ምርት ጥቅም እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ከሰል እና እንጨት መሳይ ማገዶ በመቀየር ለኃይል ምንጭነት እንዲውሉ ለበርበሬ ወረዳ ወጣቶች ድጋፍ የተደረገው ሦስት ማሽኖች የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ማሽኖቹ የቡና አምራች ገበሬዎች ተረፈ ምርቱን ለማስወገድ ያወጡ የነበረውን ወጭ ያስቀራል ብለዋል።
ተረፈ ምርቱ ለብዙ ጊዜ ተከማችቶ ከቆየ ስለሚበሰብስ ሽታው ለመተንፈሻ አካል ችግር እንደሚዳርግ አመልክተው፤ ማሽኖቹ በዚህ በኩል ያለውን ችግር እንደሚያቃልል ነው የተናገሩት።
የቡና ቅርፊትና ገለባን በግብዓትነት በመጠቀም የሚመረተው ከሰልና እንጨት መሳይ ማገዶ በቤት ውስጥ ቡና ማፍያ፣ በመንገድ ላይ ቡና ጠጡ ለሚሰሩ ሴቶች፣ ለሆቴሎችና ለሬስቶራንቶች ለምግብ ማብሰያ አገልግሎት እንደሚውልም ገልጸዋል።
አምራቹ አርሶ አደር የቡና ተረፈ ምርቶችን ለማስወገድ የሚያቃጥልበት ሁኔታ የአካባቢ ብክለትን እንደሚያስከትል ገልጸው፤ በአካባቢው በሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደኖች ላይ እየደረሰ የሚገኛውን የደን ጭፍጨፋ በመቀነስ በኩልም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል አብዱ ከድር በሰጠው አስተያየት ማሽኑ በአካባቢያቸው ላይ የሚገኘውን ተረፈ ምርት በግብዓትነት የሚጠቀም በመሆኑ የአቅርቦት ስጋት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂው በመጠቀም ራሷን በአጭር ጊዜ ለመለወጥ እንዳነሳሳት ወጣት ሰሚራ በከር ገልጻለች።
በባሌ ዞን ከ53 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ከ280 ሺህ ቶን የቡና ተረፈ ምርት ምንም ጥቅም ላይ ሳይውል በየዓመቱ እንደሚወገድ ከ'ዩኒየኑ' የተገኘው መረጃ ያመላክታል።