በኢትዮጵያን በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ተ.መ.ድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያን በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ተ.መ.ድ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 በኢትዮጵያን በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሀና ቴት ገለጹ።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ዋና ጸኃፊ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ቴት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ተስፋና እድል ያለው ክልል ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት በቀጣናው መረጋጋት ለማስፈንና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የጸጥታ ችግር መንስዔዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የድርጅቱ ትኩረትም በቀጣናው ያሉ አባል አገራት በልማት ሥራዎችና በምጣኔ ኃብት ግቦች ላይ እንዲያተኩሩ መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛዋ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ፅህፈት ቤታቸው ታዛቢ እንደነበር ጠቅሰው 'የሰላሙን ሁኔታ አሁንም መከታተላችንን እንቀጥላለን' ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍም በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች እየቀረበ መሆኑን ገልጸው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በቀጣይም መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ሥራዎች ለመደገፍ የገንዘብና የግብዓት ድጋፍ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ሰላም እንዲጠናከርና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማጠናከር እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የሰላም ሂደት የሚደነቅና ተስፋ ሰጭ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የምጣኔ ኃብታዊ ትስስርን ለማጎልበት እየሰራች ያለውን ሥራ የሚበረታታና መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።