በአማራ ክልል ከ140 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል--የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ140 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል--የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ140 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የልማት ሥራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራና የለሙ ተፋሰሶች ጉብኝት እየተካሄደ ነው።
የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የበጋ ወራት በ8ሺህ 458 ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ካለፈው ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ አርሶ አደሩ ስራውን በተሻለ ጥራት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወራት በ310 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ልማቱን ለማከናወን መታቀዱን የገለጹት ኃላፊው፣ "እስካሁንም 140 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል" ብለዋል።
ቀሪውን መሬት እስከ የካቲት ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በጥራት ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዶክተር ኃይለማርያም በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ሥራ ለምነቱ ተሟጦ የነበረው መሬት ወደነበረበት እንዲመለስና መርታማነት እዲያድግ አድርጓል።
በተለያዩ አካባቢዎች ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው መፍለቃቸውም ለመስኖ ልማት ሥራው ተጨመሪ አቅም እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ "ወተበት" ተፋሰስ ላይ በተካሄደ የለማ ተፋሰስ ጉብኝት እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ከክልልና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እተሳተፉ ነው።
በአማራ ክልል ባለፋት ዓመታት ከ7 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ አብዛኛው የለማ መሬት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የቢሮው መረጃ ያመለክታል።