የጤና መድህን አገልግሎት ህመማችን ሳይባባስ ወደ ጤና ተቋማት ሄደን የምንታከምበትን ዕድል ፈጥሮልናል- ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎት ህመማችን ሳይባባስ ወደ ጤና ተቋማት ሄደን የምንታከምበትን ዕድል ፈጥሮልናል- ተጠቃሚዎች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 የጤና መድህን አገልግሎት ህመማችን ሳይባባስ ወደ ጤና ተቋማት ሄደን የምንታከምበትን ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ከተጀመረ 10 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይነገራል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች እንደሚሉት ህመም ሲያጋጥማቸው ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋማት ባለመሄዳቸው ለችግር ይጋለጡ ነበር።
በልደታ ክፍለ ከተማ በህዳሴ ፍሬ ጤና ጣቢያ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ዘነበች በፍቃዱ፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የአባልነት ምዝገባ ያደረጉት በ2009 ዓ.ም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውና እሳቸውን እና አራት ልጆቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ህመም ሲያጋጥማቸው ያለምንም ወጪ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህክምና የሚያገኙበትን ዕድል መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
የጤና መድህን አገልግሎት እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ህመም ሲያጋጥማቸው ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንደረዳቸው አክለዋል።
የሁለት ልጆች እናት የሆኑትና የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን የሰው እጅ በመጠበቅ እንደሚገፉ የሚናገሩት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ በበኩላቸው ቀደም ሲል ከፍለው መታከም ባለመቻላቸው ይቸገሩ እንደነበር ነው ያስታውሱት።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተመቻቸው የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ በመሆናቸው የጤና እክል ሲገጥማቸው ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ህመም ሲሰማቸው የምከፍለው አጣሁ ብሎ መጨነቅ ቀንሶልናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መንግስት ቢያመቻች የተሻለ ነው ብልዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በተዘረጋው አሰራር የተሻለ የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው የመድሃኒት አቅርቦት እንዲሻሻል አያይዘው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ ለመሆን ያላቸው ፍላጎት እየጎለበተ እንደመጣ ገልፀዋል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ ስራ ከጀመረ ዓመታትን ማስቆጠሩን በመግለፅ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ 50 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው እና ጡረተኛውን ያካተተ አለመሆኑን በመናገር በቀጣይ በ2016 በጀት ዓመት እነሱን የጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ እተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፍሬህይወት ገለጻ የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ የሆኑ አባላቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የማስቻል ትልቅ ሙያዊ ግዴታ አለብን ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከመድሃኒት መጣት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ አባላት በህክምና የሚታዘዝላቸውን መድሃኒት የሚያገኙበት የማህረሰብ አቀፍ መድሃኒት ቤቶችን በተለያዩ ክልሎች እንዲኖሩ የማድረግ ስራ በመስራት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በክልሎች ከጥር ወር ጀምሮ እስከ የካቲት 30 ድረስ የሚቆይ የጤና መድህን አገልግሎት የአባልነት ምዝገባ እና እድሳት በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ምዝገባ እንዲያካሄዱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አያይዘውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ብሎ ምዝገባውን አከናውኖ መጨረሱን ጠቁመዋል፡፡