ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ቪዚት ኢትዮጵያ” የተሰኘ የቱሪዝም ካርድ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጥ "ቪዚት ኢትዮጵያ '' የተሰኘ የቱሪዝም ካርድ ይፋ አደረገ፡፡

በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎችና የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ እንግዶች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ባንኮችና ሌሎች ተቋማት የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ተቋማቱ አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት እንግዶቹ በሚያርፉባቸው ሆቴሎች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ሕብረት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ መነን ሰሙንጉሥ ፤በህብረቱ ጉባዔ ላይ ለሚሳተፉ እንግዶች የምንዛሪ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጉባዔውን ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች በተመሳሳይ በልዩ ዴስክ በመስተናገድ ላይ መሆናቸውንም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ የህብረቱ ጉባኤ አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ተሳታፊዎች ያለምንም መጉላላት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸውም አንስተዋል።

በባንኩ ባለሙያዎች እየተሰጡ ካሉ አገልግሎቶች በተጨማሪም በኤ.ቲ .ኤም ማሽኖችም የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቱሪዝም አገልግሎት ብቻ የሚውል የቱሪስት ቪዛ ካርድ ይፋ ማድረጉን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

“ ቪዛ ካርዱ እንግዶቹ ስብሰባውን ካጠናቀቁ በኋላ በኢትዮጰያ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲሄዱ የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥማቸው የሚያደርግ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

የቱሪስት ቪዛ ካርዱን በአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ለሚሳተፉ እንግዶች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የቱሪዝም ቪዛ ካርዱ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች በሀገራቸው ካለ የሂሳብ ቁጥር ጋር አስተሳስረው በመጠቀም አገልግሎት ማግኝት የሚችሉበት እንደሆነም አንስተዋል።

ጎብኚዎች ያለምንም የደህንነት ስጋት በፈለጉት አካባቢ ገንዘብ ማግኘት የሚስችላቸው መሆኑንም አክለዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በሚያርፉባቸው አካባቢዎችና በጉባኤው ቦታ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎችና ሀብቶች ይበልጥ የሚተዋወቁበት እድልን ማስፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም