ለክልላችንና ለአገራችን ልማት መፋጠን የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን - የደምቢዶሎና አካባቢው ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለክልላችንና ለአገራችን ልማት መፋጠን የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን - የደምቢዶሎና አካባቢው ነዋሪዎች
ጊምቢ ግንቦት 12/2010 የክልሉንና የሃገሪቱን ልማት ለማፋጠን በሚደረግ ጥረት ከአስፈፃሚ አካላት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የደምቢዶሎና አካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ። የነዋሪቹ ተወካዮች በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አህመድ ለሚያራምዱት የለውጥ ሃሳቦች ተግባራዊነት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። እንዲሁም ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልፀዋል፡፡ የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ አቶ ዱላ ሩንዴ በሰጡት አስተያየት ''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ለማገልገል ቃል እንደገቡ ሁሉ እኛም ከጎናቸው በመቆም ለዓላማቸው መሳካት የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን'' ብለዋል። ወይዘሮ ዘነበች ወልደየስ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት መስጠታቸው ሴቶች ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ ሃይል ስለመሆናቸው የበለጠ ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም ለክልሉና ለአገሪቱ እድገት መፋጠን ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን በትጋት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ ወጣት ፍቃዱ ፉፋ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር አንድነት፣ ለዲሞክራሲና ለዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት ለጀመሩት ትግል ስኬታማነት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ በተለይ የደምቢዶሎ ከተማ ወጣት የልማት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያደርገው ትግል በሰላማዊ መንገድ በማስቀጠል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚቆም ተናግሯል። ከሰዮ ወረዳ የመጡት የአገር ሽማግሌ አባገዳ መኮንን ቶላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር መደሰታቸውን ገልፀው ህብረተሰቡን የልማትና ዲሞክራሲ ዓላማ ከግብ እንዲደርስ መካሪ አባት በመሆንና በቻሉት ሁሉ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል። ደምቢዶሎ ከተማ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲጎበኛት ይህ የመጀመሪያው ነው።