የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሊከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሊከፍት ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ጸሀፊ ማማዱ ቢተይ ኦቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱን ለመክፈት በሚያስፈልጉ መብትና ግዴታዎች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1991 የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም የሰው ሀይልና ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት በአፍሪካ መልካም አስተዳደር ማስፈንና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ነው።
የፋውንዴሽኑ ዋና ጸሀፊ ማማዱ ቢተይ ኦቢ እንዳሉት፣ በአባል አገራቱ መካከል ዕድገትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማገዝ ከ2023 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቷል።
የአየር ንብረት ለውጥና ኢነርጂ፣ የኢኮኖሚ አስተዳደር፣ አግሪቢዝነስና የምግብ ዋስትና እና ንግድ ስትራቴጂክ ዕቅዱ የያዛቸው ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ህብረት ስር የተቋቋመው ይሄው ፋውንዴሽን ዋና መቀመጫውን ዚምባብዌ አድርጎ በጋናና ኬንያ ክልላዊ ቢሮዎች እንዳሉት ገልጸው በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ቢሮ መከፈቱ ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል።
የተቋሙን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ ተፈፃሚነት ዕውን ለማድረግም የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ቢሮ መከፈት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ተቋሙ በአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መከፈቱ የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ በተሟላ ቁመና አገልግሎት መስጠት እንዲችል የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።